መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትዳር ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ከፈጠረ በኋላ በጋብቻ አጣመራቸው። አምላክ ጋብቻን ያቋቋመው በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚመሠረት ልዩ ጥምረት እንዲሆን ነው፤ ይህ ጥምረት ለቤተሰብ መሠረት ይሆናል።—ዘፍጥረት 1:27, 28፤ 2:18
አምላክ ባለትዳሮች ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋል። (ምሳሌ 5:18) ለጋብቻ ያወጣቸውን መሥፈርቶች እንዲሁም የተሳካ ትዳር ለመመሥረት የሚረዱ መመሪያዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል።
በዚህ ርዕስ ውስጥ
አምላክ ለጋብቻ ያወጣው መሥፈርት ምንድን ነው?
ከመጀመሪያው አንስቶ፣ አምላክ ጋብቻን ያቋቋመው በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚመሠረት ጥምረት እንዲሆን ነው። (ዘፍጥረት 2:24) አምላክ ከአንድ በላይ ማግባትን፣ ግብረ ሰዶምን ወይም ሳይጋቡ አብሮ መኖርን አይፈቅድም። (1 ቆሮንቶስ 6:9፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3) ኢየሱስ ተከታዮቹ አምላክ መጀመሪያ ላይ ለትዳር ያወጣውን መሥፈርት እንዲከተሉ አስተምሯቸዋል።—ማርቆስ 10:6-8
አምላክ ትዳር ዘላቂ ጥምረት እንዲሆን ይፈልጋል። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ትዳር ሲመሠርቱ አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ለመሆን እንዲሁም በሕይወት እስካሉ ድረስ አብረው ለመኖር ቃል ይገባሉ። አምላክ ይህን ቃላቸውን እንዲያከብሩ ይጠብቅባቸዋል።—ማርቆስ 10:9
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለያየትና ስለ ፍቺ ምን ይላል?
ባልና ሚስት ተለያይተው ለመቆየት የሚገደዱበት ጊዜ ይኖራል፤ ለምሳሌ አንዳቸው ድንገተኛ የቤተሰብ ጉዳይ አጋጥሟቸው ወደ ሌላ ቦታ ሊሄዱ ይችላሉ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በትዳር ችግር ምክንያት መለያየትን አይደግፍም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ዓይነት ችግር ያጋጠማቸው ባለትዳሮች ለመታረቅ ጥረት እንዲያደርጉ ያበረታታል።—1 ቆሮንቶስ 7:10
መጽሐፍ ቅዱስ ፍቺን የሚፈቅደው ምንዝር ከተፈጸመ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 19:9) በመሆኑም አንድ ባልና ሚስት ከምንዝር ውጭ በሌላ ምክንያት ለመለያየት ወይም ለመፋታት ቢወስኑ ሁለቱም ከሌላ ሰው ጋር ለመጠናናት ወይም ድጋሚ ለማግባት ቅዱስ ጽሑፋዊ ነፃነት አይኖራቸውም።—ማቴዎስ 5:32፤ 1 ቆሮንቶስ 7:11
ጋብቻ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሕጋዊ በሆነ መንገድ መመዝገብ ይኖርበታል?
መጽሐፍ ቅዱስ ባሎችና ሚስቶች ስላላቸው ኃላፊነትና ሚና ምን ይላል?
የጋራ ኃላፊነቶች። ባልና ሚስት አንዳቸው ሌላውን በፍቅርና በአክብሮት መያዝ አለባቸው። (ኤፌሶን 5:33) አንዳቸው የሌላውን ፆታዊ ፍላጎት ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ማርካት ይኖርባቸዋል፤ በተጨማሪም በማንኛውም መልኩ ታማኝነታቸውን ማጓደል የለባቸውም። (1 ቆሮንቶስ 7:3፤ ዕብራውያን 13:4) ልጆች ከወለዱ ደግሞ ልጆቻቸውን የማሳደግ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው።—ምሳሌ 6:20
በትዳር ውስጥ፣ ከቤት ውስጥ ሥራና ከውጭ ሥራ ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት የሥራ ክፍፍል ሊኖር እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ በዝርዝር አይናገርም። ባልና ሚስቱ ለቤተሰባቸው የሚበጀውን አብረው መወሰን ይችላሉ።
የባል ሚና። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ባል የሚስቱ ራስ’ እንደሆነ ይናገራል። (ኤፌሶን 5:23) ባል ራስ የተባለው ቤተሰቡን የመምራት እንዲሁም ባለቤቱንና ልጆቹን የሚጠቅም ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት ስላለበት ነው።
የቤተሰቡን አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ከባለቤቱ ጋር ተባብሮ በመሥራት እንዲሁም ውሳኔ ሲያደርግ የእሷን ስሜትና አመለካከት ግምት ውስጥ በማስገባት የሚስቱን ችሎታና ብቃት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ማሳየት ይችላል። (ምሳሌ 31:11, 28) ባል ኃላፊነቱን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ መወጣት እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ቆላስይስ 3:19
የሚስት ሚና። መጽሐፍ ቅዱስ “ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር” ይላል። (ኤፌሶን 5:33) ሚስት፣ አምላክ ለባሏ የሰጠውን ኃላፊነት ስታከብር አምላክ ይደሰታል።
የሚስት ሚና ባሏን መደገፍ ነው፤ ባሏ ጥሩ ውሳኔዎችን እንዲያደርግ መርዳት እንዲሁም የራስነት ሥልጣኑን ማክበር ይኖርባታል። (ዘፍጥረት 2:18) በትዳር ውስጥ ያላትን ወሳኝ ሚና በሚገባ የምትወጣ ሚስትን መጽሐፍ ቅዱስ አድንቆ ይናገራል።—ምሳሌ 31:10
አምላክ በዛሬው ጊዜ ያሉ ባለትዳሮች ልጆች እንዲወልዱ ይጠብቅባቸዋል?
አይጠብቅባቸውም። በጥንት ዘመን አምላክ አንዳንድ አገልጋዮቹን ልጆች እንዲወልዱ አዟቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28፤ 9:1) ሆኖም ይህ ትእዛዝ ለክርስቲያኖች አይሠራም። ኢየሱስ ተከታዮቹን ልጆች እንዲወልዱ አዟቸው አያውቅም። ጥንት የነበሩ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ባለትዳሮች ልጆች መውለድ እንዳለባቸው ተናግረው አያውቁም። ልጅ መውለድ ይፈልጉ እንደሆነ መወሰን ያለባቸው ባለትዳሮቹ ራሳቸው ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ ለትዳሬ የሚጠቅመኝ እንዴት ነው?
ጥንዶች ትዳራቸው ጥሩ ጅምር እንዲኖረው የሚረዱ መመሪያዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያገኛሉ። በተጨማሪም ባለትዳሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች የሚከተሉ ከሆነ ከተለያዩ ችግሮች መዳን ወይም ተቋቁመው ማለፍ ይችላሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ባለትዳሮች የሚከተሉትን ነገሮች እንዲያደርጉ ይረዷቸዋል፦
a በባሕላዊ ሥርዓት ወይም በጎሳ ልማድ መሠረት የሚፈጸም ጋብቻን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅ የጥቅምት 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 21 አንቀጽ 12ን ተመልከት።