አዳምና ሔዋን የሠሩት ኃጢአት ምን ነበር?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ኃጢአት የፈጸሙት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አዳምና ሔዋን ናቸው። አዳምና ሔዋን “ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ” በመብላት የአምላክን ትእዛዝ በጣሱበት ወቅት ኃጢአት ሠርተዋል። a (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:6፤ ሮም 5:19) ዛፉ፣ አምላክ መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ለሰው ልጆች ለመወሰን ያለውን ሥልጣን ወይም መብት የሚያመለክት በመሆኑ አዳምና ሔዋን ከዛፉ ፍሬ መብላት አልተፈቀደላቸውም። አዳምና ሔዋን ፍሬውን መብላታቸው መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ለራሳቸው ለመወሰን መምረጣቸውን ያሳያል። በዚህ መልኩ፣ አምላክ ያለውን የሥነ ምግባር መሥፈርት የማውጣት ሥልጣን ለመቀበል አሻፈረኝ ብለዋል።
አዳምና ሔዋን ኃጢአት መሥራታቸው ምን ውጤት አስከትሎባቸዋል?
አዳምና ሔዋን ኃጢአት መሥራታቸው እርጅናና ሞት አስከትሎባቸዋል። ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት ያበላሹ ከመሆኑም ሌላ ፍጹም ጤናማ ሆነው ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን አጥተዋል።—ዘፍጥረት 3:19
አዳምና ሔዋን የሠሩት ኃጢአት በእኛ ላይ ምን ውጤት አስከትሏል?
አንዳንድ በሽታዎችና እክሎች ከወላጅ ወደ ልጅ በዘር እንደሚተላለፉት ሁሉ አዳምና ሔዋንም ኃጢአትን ወደ ዘሮቻቸው በሙሉ አስተላለፉ። (ሮም 5:12) በዚህም ምክንያት ሁሉም ሰዎች የሚወለዱት “በኃጢአት” b ነው፤ ይህም ሲባል ሁላችንም ከተወለድንበት ጊዜ አንስቶ ፍጽምና የሚጎድለን ከመሆናችንም ሌላ ስህተት መሥራት ይቀናናል ማለት ነው።—መዝሙር 51:5፤ ኤፌሶን 2:3
ሁላችንም ኃጢአትን ወይም አለፍጽምናን ስለወረስን እንታመማለን፣ እናረጃለን እንዲሁም እንሞታለን። (ሮም 6:23) በተጨማሪም ራሳችንም ሆንን ሌሎች ሰዎች በሚሠሩት ስህተት ምክንያት ጉዳት ይደርስብናል።—መክብብ 8:9፤ ያዕቆብ 3:2
አዳምና ሔዋን የሠሩት ኃጢአት ካስከተለው ጉዳት ነፃ መሆን እንችላለን?
በሚገባ። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ “ለኃጢአታችን የማስተሰረያ መሥዋዕት” ሆኖ እንደሞተ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 4:10) የኢየሱስ መሥዋዕት በዘር የወረስነው ኃጢአት ካስከተለብን ውጤት ነፃ ሊያወጣን ብሎም አዳምና ሔዋን ያጡትን ፍጹም ጤናማ ሆኖ ለዘላለም የመኖር ተስፋ መልሶ ሊያስገኝልን ይችላል።—ዮሐንስ 3:16 c
አዳምና ሔዋን የሠሩትን ኃጢአት በተመለከተ የሚነገሩ የተሳሳቱ አመለካከቶች
የተሳሳተ አመለካከት፦ ከአዳምና ከሔዋን የወረስነው ኃጢአት ከአምላክ ሙሉ በሙሉ ያርቀናል።
እውነታው፦ አምላክ አዳምና ሔዋን ለሠሩት ኃጢአት እኛን አይጠይቀንም። ፍጹማን እንዳልሆንን ያውቃል፤ እንዲሁም አቅማችን ከሚችለው በላይ አይጠብቅብንም። (መዝሙር 103:14) በወረስነው ኃጢአት ምክንያት መጥፎ ነገሮች የሚደርሱብን ቢሆንም እንኳ አምላክ ከእሱ ጋር የቅርብ ወዳጅነት የመመሥረት መብት ሰጥቶናል።—ምሳሌ 3:32
የተሳሳተ አመለካከት፦ አንድ ሰው ሲጠመቅ ከአዳም ከወረሰው ኃጢአት ነፃ ይወጣል፤ በመሆኑም ጨቅላ ሕፃናት መጠመቅ አለባቸው።
እውነታው፦ ጥምቀት መዳን ለማግኘት የሚረዳ ወሳኝ እርምጃ ቢሆንም አንድን ሰው ከኃጢአት ሊያነጻው የሚችለው በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ ያለው እምነት ብቻ ነው። (1 ጴጥሮስ 3:21፤ 1 ዮሐንስ 1:7) እውነተኛ እምነት ደግሞ የሚመሠረተው በእውቀት ላይ ስለሆነ ጨቅላ ሕፃናት እምነት ሊያዳብሩ አይችሉም። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ የጨቅላ ሕፃናትን ጥምቀት አይደግፍም። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁኔታም ይህን ያረጋግጣል። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ያጠምቁ የነበረው ሕፃናትን ሳይሆን በአምላክ ቃል ላይ እምነት የነበራቸውን ‘ወንዶችና ሴቶች’ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 2:41፤ 8:12
የተሳሳተ አመለካከት፦ የተከለከለውን ፍሬ መጀመሪያ የበላችው ሔዋን ስለሆነች አምላክ ሴቶችን ረግሟቸዋል።
እውነታው፦ አምላክ የረገመው ሴቶችን ሳይሆን ሔዋን ኃጢአት እንድትሠራ ያነሳሳትን “ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ” ነው። (ራእይ 12:9፤ ዘፍጥረት 3:14) በተጨማሪም አምላክ ለዚህ ኃጢአት በዋነኝነት ተጠያቂ ያደረገው አዳምን እንጂ ሚስቱን አይደለም።—ሮም 5:12
ታዲያ አምላክ አዳም ሚስቱን እንደሚገዛት የተናገረው ለምንድን ነው? (ዘፍጥረት 3:16) አምላክ ይህን የተናገረው ባሎች ሚስቶቻቸውን መጨቆናቸው ተገቢ እንደሆነ ለመግለጽ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኃጢአት በወንዶችና በሴቶች መካከል ባለው ግንኙነት ላይ የሚፈጥረውን መጥፎ ተጽዕኖ መናገሩ ነበር። አምላክ ወንዶች ሚስቶቻቸውን እንዲወዱና እንዲያከብሩ ብሎም ለሁሉም ሴቶች አክብሮት እንዲያሳዩ ይጠብቅባቸዋል።—ኤፌሶን 5:25፤ 1 ጴጥሮስ 3:7
የተሳሳተ አመለካከት፦ አዳምና ሔዋን የፈጸሙት ኃጢአት የፆታ ግንኙነት ነው።
እውነታው፦ አዳምና ሔዋን የፈጸሙት ኃጢአት የፆታ ግንኙነት ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም፦
አምላክ አዳምን ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ እንዳይበላ ያዘዘው ገና ብቻውን እያለ ነው፤ በወቅቱ ሚስት አልነበረውም።—ዘፍጥረት 2:17, 18
አምላክ አዳምንና ሔዋንን “ብዙ ተባዙ” በማለት ልጆች እንዲወልዱ አዟቸዋል። (ዘፍጥረት 1:28) አምላክ እሱ ያዘዛቸውን ነገር በመፈጸማቸው ምክንያት እነዚህን ባልና ሚስት ቢቀጣቸው ጭካኔ ይሆናል።
አዳምና ሔዋን ኃጢአት የሠሩት ለየብቻ ነው፤ መጀመሪያ ሔዋን፣ በኋላም አዳም ኃጢአት ሠርተዋል።—ዘፍጥረት 3:6
መጽሐፍ ቅዱስ ባልና ሚስት የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ይፈቅዳል።—ምሳሌ 5:18, 19፤ 1 ቆሮንቶስ 7:3
a ብዙ ሰዎች አዳምና ሔዋን የሠሩት ኃጢአት የመጀመሪያው ኃጢአት እንደሆነ ያምናሉ። ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የመጀመሪያው ኃጢአት ሰይጣን ለሔዋን የተናገረው የማታለያ ንግግርና ዓይን ያወጣ ውሸት ነው።—ዘፍጥረት 3:4, 5፤ ዮሐንስ 8:44
b በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ኃጢአት” የሚለው ቃል መጥፎ ድርጊቶችን ብቻ ሳይሆን በዘር የወረስነውን አለፍጽምናም ያመለክታል።
c ስለ ኢየሱስ መሥዋዕት እንዲሁም ከመሥዋዕቱ ጥቅም ማግኘት ስለምንችልበት መንገድ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ኢየሱስ ያድናል—እንዴት?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።