መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ በላይ ማግባትን ይደግፋል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አምላክ፣ ሰዎች ከአንድ በላይ እንዲያገቡ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ፈቅዶ ነበር። (ዘፍጥረት 4:19፤ 16:1-4፤ 29:18-29) ይሁንና ከአንድ በላይ የማግባትን ልማድ ያስጀመረው አምላክ አይደለም። ለአዳም የሰጠው አንዲት ሚስት ብቻ ነው።
አምላክ፣ አንድ ወንድ አንዲትን ሴት ብቻ እንዲያገባ የነበረውን ዓላማ ኢየሱስ ክርስቶስ በድጋሚ ለሰዎች እንዲገልጽ አድርጓል። (ዮሐንስ 8:28) ኢየሱስ ስለ ትዳር ጥያቄ ሲቀርብለት እንዲህ የሚል መልስ ሰጥቷል፦ “ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁም? ‘በዚህ ምክንያት ሰው ከአባትና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።’”—ማቴዎስ 19:4, 5
ከጊዜ በኋላም ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ወንድ የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዷም ሴት የራሷ ባል ይኑራት።” (1 ቆሮንቶስ 7:2) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ያገባ ወንድ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የተለየ ኃላፊነት እንዲሰጠው “የአንዲት ሚስት ባል” መሆን እንዳለበት ይናገራል።—1 ጢሞቴዎስ 3:2, 12