የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል—መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ስሜት ለማሸነፍ ሊረዳኝ ይችላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰማንን የጥፋተኝነት ስሜት ለማሸነፍ የሚረዱ ምክሮች ይዟል። (መዝሙር 32:1-5) ስህተት ስንሠራ ከልባችን ከተጸጸትን አምላክ ይቅር ይለናል፤ እንዲሁም ወደ ቀድሞ ሁኔታችን እንድንመለስ ይረዳናል። (መዝሙር 86:5) መጽሐፍ ቅዱስ፣ የጥፋተኝነት ስሜት አንዳንድ ጊዜ ጠቃሚ እንደሆነ ይናገራል፤ ለምሳሌ ስህተታችንን እንድናርምና ለወደፊቱ ተመሳሳይ ስህተት ላለመሥራት የቻልነውን ሁሉ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይችላል። (መዝሙር 51:17፤ ምሳሌ 14:9) ያም ቢሆን ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ጎጂ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፤ ተስፋ እንደሌለን ወይም አምላክ እንደማይወደን እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል። እንዲህ ያለው ስሜት ደግሞ ‘ከልክ በላይ በሐዘን እንድንዋጥ’ እንዲሁም ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርገን ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 2:7
የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርገው ምንድን ነው?
የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ የምንወደውን ሰው በድለነው ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ማድረግ እንዳለብን የምናምንበትን ነገር ሳናደርግ ቀርተን ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ግን የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማን ያጠፋነው ነገር ሳይኖር ነው። ለምሳሌ ያህል ከራሳችን ብዙ የምንጠብቅ ከሆነ፣ ለራሳችን ያወጣነውን መሥፈርት ማሟላት ባቃተን ቁጥር የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ እንድንሆን የሚያበረታታን ለዚህ ነው።—መክብብ 7:16
የጥፋተኝነት ስሜትን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?
የጥፋተኝነት ስሜት ተስፋ እንዲያስቆርጥህ ከመፍቀድ ይልቅ ጉዳዩን ለማስተካከል የምትችለውን ሁሉ አድርግ። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ?
ስህተትህን አምነህ ተቀበል። ይቅር እንዲልህ ይሖዋ a አምላክን በጸሎት ጠይቀው። (መዝሙር 38:18፤ ሉቃስ 11:4) በሠራኸው ስህተት ከልብህ ከተጸጸትክና ስህተቱን ላለመድገም የቻልከውን ሁሉ የምታደርግ ከሆነ አምላክ ጸሎትህን እንደሚሰማ መተማመን ትችላለህ። (2 ዜና መዋዕል 33:13፤ መዝሙር 34:18) ከሰዎች በተቃራኒ አምላክ በልባችን ውስጥ ያለውን ነገር ማየት ይችላል። ስህተታችንን ላለመድገም የምናደርገውን ጥረት ሲያይ “ታማኝና ጻድቅ ስለሆነ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል።”—1 ዮሐንስ 1:9፤ ምሳሌ 28:13
የበደልከው ሰው ካለም ስህተትህን አምነህ መቀበልና ግለሰቡን ከልብ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብሃል። እንዲህ ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል! ድፍረትና ትሕትና ይጠይቃል። ሆኖም ከልብ ይቅርታ መጠየቅ ሁለት ጥቅሞች አሉት፤ አንደኛ፣ አንተ የሚሰማህን የጥፋተኝነት ስሜት ያቀልልሃል፤ እንዲሁም በመካከላችሁ የነበረው ሰላማዊ ግንኙነት እንዲመለስ ያደርጋል።—ማቴዎስ 3:8፤ 5:23, 24
ስለ አምላክ ምሕረት በሚናገሩ ጥቅሶች ላይ አሰላስል። ለምሳሌ በ1 ዮሐንስ 3:19, 20 ላይ ማሰላሰል ትችላለህ። ጥቅሱ ‘ልባችን ሊኮንነን’ እንደሚችል ይናገራል፤ በሌላ አባባል ‘አምላክ አይወደኝም’ ብለን በራሳችን ላይ ልንፈርድ እንችላለን። ሆኖም ጥቅሱ “አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው” በማለትም ይናገራል። እንዲህ ሲባል ምን ማለት ነው? አምላክ ስለ እኛ ሁሉንም ያውቃል፤ ስሜታችንንና ድክመቶቻችንን በደንብ ይረዳል። በተጨማሪም ስንወለድ ጀምሮ ፍጹም እንዳልሆንን እንዲሁም ስህተት መሥራት እንደሚቀናን ያውቃል። b (መዝሙር 51:5) በመሆኑም አምላክ፣ በሠሩት ጥፋት ከልብ ያዘኑ ሰዎችን አይጠላቸውም።—መዝሙር 32:5
የሠራኸውን ስህተት እያሰብክ አትብሰልሰል። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ፣ በሆነ ወቅት ስህተት የሠሩ በኋላ ግን አካሄዳቸውን ያስተካከሉ ወንዶችና ሴቶች ተጠቅሰዋል። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ፣ በኋላ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ የተጠራው የጠርሴሱ ሳኦል ነው። ጳውሎስ ፈሪሳዊ በነበረበት ወቅት በኢየሱስ ተከታዮች ላይ ከባድ ስደት ያደርስ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 8:3፤ 9:1, 2, 11) እየተቃወመ ያለው አምላክንና መሲሑን ማለትም ክርስቶስን እንደሆነ ሲገነዘብ ግን በድርጊቱ ተጸጸተ፤ ንስሐ ገባ፤ እንዲሁም ጥሩ ክርስቲያን ሆነ። ጳውሎስ ቀደም ሲል በፈጸመው ስህተት የተነሳ በጣም ቢያዝንም ስለ ስህተቱ ነጋ ጠባ እያሰበ አልተብሰለሰለም። አምላክ ታላቅ ምሕረት እንዳሳየው ስለተገነዘበ በትጋት ይሰብክ ነበር፤ እንዲሁም ምንጊዜም ትኩረት ያደረገው በዘላለም ሕይወት ተስፋው ላይ ነበር።—ፊልጵስዩስ 3:13, 14
ስለ ጥፋተኝነት ስሜትና ስለ ይቅርታ የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች
መዝሙር 51:17፦ “አምላክ ሆይ፣ የተሰበረንና የተደቆሰን ልብ ችላ አትልም።”
ምን ማለት ነው? አምላክ፣ በእሱ ላይ በሠራኸው በደል ከልብህ ካዘንክ በስህተትህ የተነሳ አይጠላህም። ምሕረት ያደርግልሃል።
ምሳሌ 28:13፦ “የሠራውን በደል የሚሸፋፍን አይሳካለትም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ሁሉ ግን ምሕረት ያገኛል።”
ምን ማለት ነው? ኃጢአታችንን ለአምላክ ከተናዘዝንና አካሄዳችንን ካስተካከልን አምላክ ይቅር ይለናል።
ኤርምያስ 31:34፦ “በደላቸውን ይቅር እላለሁና፤ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስታውስም።”
ምን ማለት ነው? አምላክ አንዴ ይቅር ካለን ስህተታችንን እንደገና አያነሳብንም። የእሱ ምሕረት እውነተኛ ነው።
b በተፈጥሯችን ስህተት የሆነውን ነገር ማድረግ የሚቀናን የመጀመሪያው ሰው አዳም ኃጢአትን ስላወረሰን ነው። አዳምና ሚስቱ ሔዋን በአምላክ ላይ ኃጢአት ሠሩ፤ በውጤቱም አዳም ፍጹም የሆነ ሕይወቱን አጣ፤ ዘሮቹንም እንዲህ ዓይነት ሕይወት የማግኘት አጋጣሚያቸውን አሳጣቸው።—ዘፍጥረት 3:17-19፤ ሮም 5:12