የ666 ትርጉም ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ እንደሚጠቁመው ይህ ቁጥር፣ ከባሕር የወጣው እንዲሁም አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ያሉት አውሬ ቁጥር ወይም ስም ነው። (ራእይ 13:1, 17, 18) አውሬው “በነገድ፣ በሕዝብ፣ በቋንቋና በብሔር ሁሉ ላይ” ሥልጣን የተሰጠውን በዓለም ላይ ያለውን አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓት የሚወክል ነው። (ራእይ 13:7) አውሬው 666 የተባለ ቁጥር የተሰጠው መሆኑ ደግሞ አውሬውን የሚወክለው የፖለቲካ ሥርዓት በአምላክ ዓይን ሲታይ በከፍተኛ ሁኔታ እንከን ያለበት መሆኑን ያመለክታል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
ቁጥሩ መጠሪያ ብቻ አይደለም። አምላክ የሚሰጣቸው ስሞች ከመጠሪያነት ባለፈ ትርጉም ያላቸው ናቸው። ለምሳሌ አምላክ፣ የአብራም ስም (“አባት ተከበረ” ማለት ነው) ተቀይሮ አብርሃም (“የብዙ ሕዝቦች አባት” ማለት ነው) ተብሎ እንዲጠራ አድርጓል፤ አምላክ ይህን ስም የሰጠው አብርሃምን “የብዙ ሕዝቦች አባት” እንደሚያደርገው ቃል በገባለት ወቅት ነው። (ዘፍጥረት 17:5) በተመሳሳይም አምላክ ለአውሬው ያወጣው 666 የሚለው ስም አውሬው ምን ባሕርይ እንዳለው የሚያመለክት መግለጫ ነው።
ስድስት ቁጥር እንከንን ያመለክታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ቁጥሮች አብዛኛውን ጊዜ ምሳሌያዊ ትርጉም አላቸው። ሰባት ቁጥር አንድ ነገር የተሟላ ወይም ፍጹም መሆኑን ያመለክታል። ስድስት ደግሞ ከሰባት በአንድ ስለሚያንስ አንድ ነገር በአምላክ ዓይን ሲታይ ጉድለት ወይም እንከን እንዳለበት ይጠቁማል፤ ቁጥሩ ከአምላክ ጠላቶች ጋር ተያይዞ የተሠራበት ወቅትም አለ።—1 ዜና መዋዕል 20:6፤ ዳንኤል 3:1
ሦስት ጊዜ መደጋገም አንድን ነገር ለማጉላት ይሠራበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድን ነገር ለማጉላት ሐሳቡ ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ የተጠቀሰባቸው ጊዜያት አሉ። (ራእይ 4:8፤ 8:13) በመሆኑም 666 በሚለው ቁጥር ላይ ስድስት ቁጥር ሦስት ጊዜ መደጋገሙ የሰዎች አገዛዝ በአምላክ ዓይን ሲታይ ከፍተኛ እንከን እንዳለበት የሚያጎላ ነው። እነዚህ ሰብዓዊ መንግሥታት ለሰው ልጆች ዘላቂ የሆነ ሰላም እንዲሁም ደኅንነት ማምጣት አልቻሉም፤ እነዚህ ነገሮች ሊያስገኝ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው።
የአውሬው ምልክት
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ሰዎች ‘የአውሬውን ምልክት’ ይቀበላሉ፤ ይህም ሰዎች ለአውሬው አምልኮ እስከ ማቅረብ ድረስ ‘በአድናቆት እንደሚከተሉት’ የሚያሳይ ነው። (ራእይ 13:3, 4፤ 16:2) ይህን የሚያደርጉት ለአገራቸው፣ ለአገራቸው ባንዲራ ወይም አርማ እንዲሁም ለወታደራዊ ኃይሉ የአምልኮ ያህል ክብር በመስጠት ነው። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን “በዘመናችን ብሔራዊ ስሜት ራሱን የቻለ ዋና ሃይማኖት ሆኗል” ብሏል። a
ታዲያ ሰዎች የአውሬውን ምልክት በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ላይ የሚያደርጉት እንዴት ነው? (ራእይ 13:16) አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ሕግጋት በተመለከተ “በእጆቻችሁ ላይ ምልክት አድርጋችሁ እሰሯቸው፣ በግምባራችሁም ላይ ይሁኑ” ብሏቸው ነበር። (ዘዳግም 11:18) ይህም ሲባል እስራኤላውያን ቃል በቃል በእጆቻቸውና በግምባራቸው ላይ ምልክት ያድርጉ ማለት አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ በድርጊታቸውም ሆነ በአስተሳሰባቸው በአምላክ ሕግጋት መመራት እንዳለባቸው የሚያሳስብ ነበር። በተመሳሳይም ሰዎች የአውሬውን ምልክት ያደርጋሉ ሲባል ሰውነታቸው ላይ 666 የሚል ምልክት እንደሚነቀሱ የሚያሳይ አይደለም፤ ሰዎች የአውሬውን ምልክት ማድረጋቸው የፖለቲካው ሥርዓት ሕይወታቸውን እንዲቆጣጠር መፍቀዳቸውን የሚጠቁም ነው። የአውሬውን ምልክት የሚያደርጉ ሰዎች የአምላክ ተቃዋሚዎች ናቸው።—ራእይ 14:9, 10፤ 19:19-21
a በተጨማሪም Nationalism in a Global Era ገጽ 134ን እንዲሁም Nationalism and the Mind: Essays on Modern Culture ገጽ 94ን ተመልከት።