የወጣቶች ጥያቄ
መጸለይ ጥቅም አለው?
አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በአሜሪካ 80 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች የሚጸልዩ ቢሆንም ከእነዚህ ወጣቶች መካከል በየዕለቱ የሚጸልዩት ግማሽ ያህሉ ብቻ ናቸው። በመሆኑም አንዳንዶች ‘ጸሎት አእምሮን ከማረጋጋት ያለፈ ጥቅም አለው?’ ብለው መጠየቃቸው ምንም አያስገርምም።
ጸሎት ምንድን ነው?
ጸሎት የሁሉ ነገር ፈጣሪ ከሆነው አምላካችን ጋር የምንነጋገርበት መንገድ ነው። ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው! ይሖዋ በማንኛውም መንገድ ከሰው ልጆች የላቀ ነው፣ ሆኖም ‘እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።’ (የሐዋርያት ሥራ 17:27) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” የሚል አስደናቂ ግብዣ ይዟል።—ያዕቆብ 4:8
ወደ አምላክ መቅረብ የምትችለው እንዴት ነው?
አንደኛው መንገድ ጸሎት ነው። ይህ አምላክን የምታነጋግርበት መንገድ ነው።
ሌላው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ነው። ይህ ደግሞ አምላክ አንተን ‘የሚያነጋግርበት’ መንገድ ነው።
ይህን የመሰለው የሐሳብ ግንኙነት ማለትም መጸለይህና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ ከአምላክ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ለመመሥረት ይረዳሃል።
‘የሰው ልጆች ካገኟቸው እጅግ የላቁ መብቶች አንዱ ከልዑሉ አምላክ ከይሖዋ ጋር መነጋገር መቻል ነው።” —ጄረሚ
“ለይሖዋ በጸሎት አማካኝነት የውስጤን አውጥቼ ስናገር ወደ እርሱ ይበልጥ እንደቀረብኩ ይሰማኛል።”—ሚራንዳ
አምላክ ጸሎቴን ይሰማል?
በአምላክ የምታምን እንዲሁም ወደ እሱ የምትጸልይ ቢሆንም እንኳ ‘በእርግጥ አምላክ ጸሎቴን ይሰማል?’ የሚል ጥያቄ ሊፈጠርብህ ይችላል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን “ጸሎት ሰሚ [የሆነ] አምላክ” በማለት ይጠራዋል። (መዝሙር 65:2) እንዲያውም “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ” በማለት ይጋብዘናል። ለምን? “ምክንያቱም እሱ ስለ [እኛ] ያስባል።”—1 ጴጥሮስ 5:7
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ከቅርብ ጓደኞችህ ጋር ዘወትር ለመገናኘት ጊዜ ትመድባለህ? ከአምላክ ጋር ለመነጋገርም እንዲሁ ማድረግ ትችላለህ። አዘውትረህ ወደ አምላክ ጸልይ፤ ይህን ስታደርግ ይሖዋ የሚለውን ስሙን ተጠቀም። (መዝሙር 86:5-7፤ 88:9) ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ “ዘወትር ጸልዩ” በማለት ጋብዞናል።—1 ተሰሎንቄ 5:17
“ጸሎት፣ የውስጤን ሁሉ አውጥቼ የምነግረውን የሰማዩን አባቴን የማነጋግርበት መንገድ ነው።”—ሞኢስስ
“ከእናቴ ወይም ከቅርብ ጓደኞቼ ጋር ስነጋገር ሐሳቤን በዝርዝር እንደምነግራቸው ሁሉ ለይሖዋም ሁሉን ነገር በዝርዝር እነግረዋለሁ።”—ካረን
ስለ ምን ነገር መጸለይ እችላለሁ?
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።”—ፊልጵስዩስ 4:6
ታዲያ ችግሮችህን በተመለከተ ልትጸልይ ትችላለህ ማለት ነው? አዎ! እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል” ይላል።—መዝሙር 55:22
ለአምላክ የምታቀርበው ጸሎት ችግሮችህን ብቻ ከመግለጽ ያለፈ መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው። ቻንቴል የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ወደ ይሖዋ የምጸልየው እንዲረዳኝ ስፈልግ ብቻ ቢሆን ኖሮ ጥሩ ወዳጅነት አለን ሊባል አይችልም ነበር። ምስጋና መቅደም እንዳለበት ይሰማኛል፤ እንዲሁም እሱን ለማመስገን የሚያነሳሱ ብዙ ነገሮች ሊኖሩኝ እንደሚገባ አምናለሁ።”
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ በሕይወትህ ውስጥ አምላክን ለማመስገን የሚያነሳሱህ ምን ነገሮች አሉ? በዛሬው ዕለት ይሖዋን እንድታመሰግነው የሚያነሳሱ ሦስት ነገሮችን ማሰብ ትችላለህ?
“የሚያምር አበባ አይቶ ማድነቅን የመሰለ ቀላል ነገር እንኳ ለይሖዋ የምስጋና ጸሎት እንድናቀርብ ያነሳሳናል።”—አኒታ
“በፍጥረት ሥራዎች ላይ ወይም ልባችሁን በሚነካ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ አሰላስሉ፣ ከዚያም ስለ ጉዳዩ ይሖዋን አመስግኑት።”—ብራያን