የወጣቶች ጥያቄ
ምትሃታዊ ነገሮች ጉዳት አላቸው?
ምን ይመስልሃል?
ኮከብ ቆጠራ ማንበብ፣ ጠንቋዮችን ማማከር ወይም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ይረዳሉ የሚባሉ መሣሪያዎችን መጠቀም ጉዳት አለው?
ምትሃታዊ ታሪኮች በጥሩ እና በመጥፎ ኃይሎች መካከል የሚደረገውን ውጊያ የሚገልጹ ምሳሌዎች ብቻ ናቸው? ወይስ አደጋ አላቸው?
ይህ ርዕስ መናፍስታዊ ነገሮች ማራኪ ሊመስሉ የሚችሉበትን ምክንያት እንዲሁም ከእነሱ መጠንቀቅ የሚኖርብህ ለምን እንደሆነ ያብራራል።
ሰዎችን የሚማርኩት ለምንድን ነው?
የመዝናኛው ኢንዱስትሪ በርካታ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ቪዲዮ ጌሞችና መጻሕፍት በምትሃታዊ ነገሮች ዙሪያ ያጠነጠኑ እንዲሆኑ አድርጓል። በመሆኑም በርካታ ወጣቶች እንደ ኮከብ ቆጠራ፣ አጋንንት፣ ቫምፓየሮችና ጥንቆላ ባሉት ነገሮች ትኩረታቸው እየተሳበ ነው። ለምን? አንዳንድ ምክንያቶችን እንመልከት፦
የማወቅ ጉጉት፦ መንፈሳዊ ፍጥረታት በእርግጥ መኖራቸውን ለማረጋገጥ።
ስጋት፦ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ።
ናፍቆት፦ የሞቱ ሰዎችን ለማነጋገር።
እነዚህ ምክንያቶች በራሳቸው ስህተት ላይሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማወቅ መፈለግ ወይም የሞተብንን ሰው መናፈቅ ተፈጥሯዊ ነው። ሆኖም ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡ አደጋዎች አሉ።
መጠንቀቅ ያለብህ ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ከመናፍስታዊ ነገሮች ጋር ንክኪ ካለው ከማንኛውም ነገር እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ይላል፦
“ሟርተኛ፣ አስማተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ምትሃተኛ፣ ድግምተኛ፣ መናፍስት ጠሪ፣ ጠንቋይ ወይም ሙታን አነጋጋሪ በመካከልህ አይገኝ። ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው ሁሉ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው።”—ዘዳግም 18:10-12
መጽሐፍ ቅዱስ መናፍስታዊ ነገሮችን አጥብቆ የሚቃወመው ለምንድን ነው?
መናፍስታዊ ነገሮች የአጋንንት ወዳጆች እንድንሆን ያበረታታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ መላእክት በአምላክ ላይ በማመፅ የእሱ ጠላቶች እንደሆኑ ያስተምራል። (ዘፍጥረት 6:2፤ ይሁዳ 6) አጋንንት ተብለው የሚጠሩት እነዚህ ክፉ መላእክት መናፍስት ጠሪዎችን፣ ጠንቋዮችንና ኮከብ ቆጣሪዎችን በመጠቀም ሰዎችን ያስታሉ። እንዲህ ባሉ ድርጊቶች መካፈል እኛም ከአምላክ ጠላቶች ጎን እንድንሰለፍ ያደርገናል።
መናፍስታዊ ነገሮች አንዳንድ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማወቅ ይችላሉ በሚለው የተሳሳተ ሐሳብ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም “ከመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ገና ያልተከናወኑትንም ነገሮች ከረጅም ጊዜ በፊት አስቀድሜ እናገራለሁ” ሊል የሚችለው እውነተኛው አምላክ ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 46:10፤ ያዕቆብ 4:13, 14
መናፍስታዊ ነገሮች ሙታን ከሕያዋን ጋር መነጋገር ይችላሉ በሚለው የተሳሳተ ሐሳብ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን . . . ምንም አያውቁም፤ . . . በመቃብር ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለም” ይላል።—መክብብ 9:5, 10
በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ የይሖዋ ምሥክሮች ከመናፍስታዊ ነገሮች ጋር ንክኪ ካለው ከማንኛውም ድርጊት ይርቃሉ። በተጨማሪም እንደ ዞምቢዎች፣ ቫምፓየሮችና ምትሃታዊ ድርጊቶች ያሉ ነገሮችን ከሚያሳዩ መዝናኛዎች ይርቃሉ። ማሪያ የተባለች ወጣት “መናፍስታዊ ነገሮች ካሉት ልመለከተው አይገባም” በማለት ተናግራለች። a
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ከምትሃታዊ ነገሮች ጋር ንክኪ ካለው መዝናኛም ሆነ ድርጊት በመራቅ በይሖዋ ፊት “ንጹሕ ሕሊና” ይዘህ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።—የሐዋርያት ሥራ 24:16
ከምትሃታዊ ነገሮች ጋር ንክኪ ያላቸውን ዕቃዎች አስወግድ። የሐዋርያት ሥራ 19:19, 20ን በማንበብ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ የተዉትን ጥሩ ምሳሌ ልብ በል።
ይህን አትርሳ፦ ምትሃታዊ ይዘት ካላቸው መዝናኛዎችና ድርጊቶች ስትርቅ ከይሖዋ ጎን እንደተሰለፍክ ታሳያለህ። ይህ ደግሞ የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኘዋል!—ምሳሌ 27:11
a ይህ ሲባል ምናባዊ ፈጠራ የሆኑ ነገሮች በሙሉ መናፍስታዊ ነገሮች ናቸው ማለት አይደለም። ይሁንና ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናቸውን ተጠቅመው ከመናፍስታዊ ነገሮች ጋር ንክኪ ካለው ከማንኛውም መዝናኛ ወይም ድርጊት ይርቃሉ።—2 ቆሮንቶስ 6:17፤ ዕብራውያን 5:14