የወጣቶች ጥያቄ
በስብሰባ አዳራሽ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ያለብኝ ለምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች አምልኳቸውን የሚያከናውኑባቸው ቦታዎች የስብሰባ አዳራሾች ተብለው ይጠራሉ፤ በእነዚህ ቦታዎች በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ ይሰበሰባሉ። ለመሆኑ በስብሰባ አዳራሾቹ ውስጥ ምን ይከናወናል? በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ስትገኝ ጥቅም ማግኘት የምትችለውስ እንዴት ነው?
በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ ምን ይከናወናል?
የስብሰባ አዳራሾች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ጠቃሚ ሐሳቦች የምንማርባቸው ቦታዎች ናቸው። በዚያ የሚደረጉት ስብሰባዎች የሚከተሉትን ጥቅሞች ያስገኙልሃል፦
ስለ አምላክ እውነቱን እንድታውቅ ያስችሉሃል።
በዛሬው ጊዜ ካሉ ሁኔታዎች በስተጀርባ ያለውን እውነታ እንድትገነዘብ ይረዱሃል።
የተሻልክ ሰው እንድትሆን ያደርጉሃል።
ጥሩ ጓደኞችን ለማፍራት የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍቱልሃል።
ይህን ታውቅ ነበር? የይሖዋ ምሥክሮች በስብሰባ አዳራሻቸው ውስጥ በዋነኝነት የሚማሩት ስለ አምላክ መንግሥት ነው።—ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14፤ ሉቃስ 4:43
በስብሰባዎቹ ላይ መገኘት ያለብህ ለምንድን ነው?
የምታገኘው ትምህርት ይጠቅምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ የምትማራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ‘ጥበብ እንድታገኝ’ ይረዱሃል። (ምሳሌ 4:5) በሌላ አነጋገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወትህ ውስጥ ጥሩ ውሳኔዎችን እንድታደርግ ሊረዳህ ይችላል። በተጨማሪም በሕይወትህ ውስጥ ለምታነሳቸው እንደሚከተሉት ላሉ አስፈላጊ ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ይረዳሃል፦
ንግግር ከሚሰጥባቸው ርዕሶች መካከል ደግሞ የሚከተሉት ይገኙበታል፦
መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያችን አድርገን ልንጠቀምበት የሚገባው ለምንድን ነው?
በመከራ ወቅት እርዳታ ከየት ማግኘት ትችላላችሁ?
የአምላክ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ምን እያደረገልን ነው?
“አብሮኝ የሚማር አንድ ልጅ በስብሰባችን ላይ ተገኝቶ ነበር። የተቀመጠው ከቤተሰቦቼ ጋር ስለነበር የምናጠናቸውን ጽሑፎች አሳየነው። ከስብሰባው በኋላ፣ አድማጮች ተሣትፎ በሚያደርጉባቸው ክፍሎች ላይ የተሰጡት ሐሳቦች በጣም እንዳስደነቁት ነገረኝ። እሱ በሚካፈልበት ቤተ ክርስቲያን ያሉ ሰዎች እኛ ያሉን ዓይነት የማጥኛ ጽሑፎች እንደሌሏቸውም ነገረኝ።”—ብሬንዳ
ይህን ታውቅ ነበር? ወደ ስብሰባ አዳራሽ ለመግባት ክፍያ አትጠየቅም፤ ሙዳየ ምጽዋትም አይዞርም።
የሚያበረታቱ ጥሩ ጓደኞች ታገኛለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች አንድ ላይ መሰብሰባቸው አስፈላጊ የሆነበት አንዱ ምክንያት ‘እርስ በርስ እንዲበረታቱ’ እንደሆነ ይናገራል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ከራሳቸው ይልቅ አምላክንና ሌሎችን ከሚያስቀድሙ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ አስደሳች ነው።
“አድካሚ ቀን ካሳለፍኩ በኋላ የምከፋባቸውና የምዝልባቸው ጊዜያት አሉ፤ ሆኖም በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ የማገኛቸው ሰዎች ያበረታቱኛል። ከስብሰባ ወደ ቤቴ የምመለሰው በጣም ተደስቼና ቀጣዩን ቀን በድፍረት ለመጋፈጥ ዝግጁ ሆኜ ነው።” —ኤሊዛ
ይህን ታውቅ ነበር? በዓለም ዙሪያ ከ60,000 በሚበልጡ ቦታዎች ስብሰባ የሚያደርጉ ከ120,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ይገኛሉ። በስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው ስለሚጨምር እነዚህ ሰዎችን ለማስተናገድ በየዓመቱ በአማካይ ወደ 1,500 የስብሰባ አዳራሾች ይገነባሉ። a
a በአቅራቢያህ ስብሰባ የሚደረግበትን ቦታ ለማግኘት “የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጓቸው ሳምንታዊ ስብሰባዎች” የሚለውን ገጽ ከከፈትክ በኋላ “ለአንተ ቅርብ የሆነውን ቦታ ፈልግ” የሚለውን ሊንክ ጠቅ አድርግ።