የወጣቶች ጥያቄ
በኢንተርኔት አማካኝነት ጥቃት ቢሰነዘርብኝ ምን ላድርግ?
ማወቅ ያለብህ ነገር
ኢንተርኔት ጥቃት መሰንዘር ቀላል እንዲሆን አድርጓል። ሳይበርሴፍ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ሰዎች “ማንነታቸው ስለማይታወቅ ጥሩ ልጆች እንኳ መጥፎ ነገር ለማድረግ ነፃነት ይሰማቸዋል።”
አንዳንድ ሰዎች ይበልጥ ተጠቂ ይሆናሉ። ይህም ዓይናፋር የሆኑ፣ ከሌሎች ለየት ብለው የሚታዩ ወይም ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅተኛ የሆነ ልጆችን ይጨምራል።
በኢንተርኔት አማካኝነት የሚሰነዘር ጥቃት አስከፊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ተጠቂዎቹ ብቸኝነት እንዲሰማቸውና በመንፈስ ጭንቀት እንዲያዙ ሊያደርግ ይችላል፤ እንዲያውም አንዳንዶች ራሳቸውን እስከመግደል ደርሰዋል።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
በመጀመሪያ “በእርግጥ ጥቃት እየተሰነዘረብኝ ነው?” ብለህ ራስህን ጠይቅ። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሳያስቡት ሌሎችን የሚጎዳ ንግግር የሚናገሩበት ጊዜ አለ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመህ የሚከተለውን ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ፦
“ቁጣ የሞኝ ሰው መለያ ስለሆነ ለቁጣ አትቸኩል።”—መክብብ 7:9 የግርጌ ማስታወሻ
በሌላ በኩል ግን አንድ ሰው በኢንተርኔት አማካኝነት ሆን ብሎ ሌላውን ሰው የሚያንቋሽሽ፣ የሚያዋርድ ወይም የሚያስፈራራ ከሆነ በእርግጥ ጥቃት እየሰነዘረ ነው ሊባል ይችላል።
በኢንተርኔት አማካኝነት ጥቃት እየተሰነዘረብህ ከሆነ ይህን አስታውስ፦ የምትሰጠው ምላሽ ሁኔታውን ሊያስተካክለው ወይም ሊያባብሰው ይችላል። ከታች ከተጠቀሱት ሐሳቦች መካከል አንዳንዶቹን ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር።
ችላ ብለህ እለፈው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አዋቂ ሰው ንግግሩ ቁጥብ ነው፤ ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰውም የተረጋጋ ነው።”—ምሳሌ 17:27
ይህ ምክር ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት፦ ናንሲ ዊላርድ የተባለች ጸሐፊ ሳይበርቡሊንግ ኤንድ ሳይበርትሬትስ በተባለው መጽሐፏ ላይ እንደገለጸችው “ጥቃት የሚሰነዝሩ ሰዎች ዋነኛ ዓላማቸው ሰዎቹ እንዲበሳጩ ማድረግ ነው። . . . የጥቃቱ ሰለባዎች የሚበሳጩ ከሆነ ጥቃት የሚሰነዝረው ሰው በስሜታቸው ላይ እንዳሻው እንዲጫወት የፈቀዱለት ያህል ይቆጠራል።”
ዋናው ነጥብ፦ አንዳንድ ጊዜ ከሁሉ የተሻለው ምላሽ ምንም ምላሽ አለመስጠት ሊሆን ይችላል።
አጸፋ አትመልስ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ አትመልሱ።”—1 ጴጥሮስ 3:9
ይህ ምክር ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት፦ ሳይበር ሴፍ ኪድስ፣ ሳይበር ሳቪ ቲንስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚናገረው “መበሳጨት የድክመት ምልክት ነው፤ ይህ ደግሞ ተጨማሪ ጥቃት እንዲሰነዘርብህ ያደርጋል።” ከዚህም በተጨማሪ፣ አጸፋ መመለስህ አንተም ለችግሩ በተወሰነ መጠን ተጠያቂ እንደሆንክ ሊያስመስል ይችላል።
ዋናው ነጥብ፦ አጸፋ መመለስ በእሳት ላይ ነዳጅ እንደመጨመር ነው።
እርምጃ ውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በክፉ አትሸነፍ።” (ሮም 12:21) ሁኔታውን ሳታባብስ የሚሰነዘርብህን ጥቃት ለማስቆም ልትወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎች አሉ።
ለምሳሌ ያህል፦
መልእክቱ እንዳይደርስህ አግድ (ግለሰቡን ብሎክ አድርግ)። ሚን ቢሃይንድ ዘ ስክሪን የተባለው መጽሐፍ “ያላነበባችሁት መልእክት ጉዳት ሊያደርስባችሁ አይችልም” ይላል።
የተላከልህን መልእክት ባታነበውም እንኳ ጥቃት እንደተሰነዘረብህ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በሙሉ አስቀምጥ። ይህም ጥቃት ለመሰንዘር ተብለው የተላኩ የጽሑፍ መልእክቶችን፣ ኢሜይሎችን፣ በብሎግ ወይም በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የወጡ ነገሮችን፣ የድምፅ መልእክቶችን ወይም ሌላ ማንኛውንም መልእክት ያካትታል።
ጥቃት ለሚሰነዝርብህ ሰው ጥቃቱን እንዲያቆም ንገረው። ጥብቅ ሆኖም ስሜታዊነት የማይንጸባረቅበት መልእክት ላክ፤ ለምሳሌ እንዲህ ማለት ትችላለህ፦
“ከዚህ በኋላ ምንም መልእክት እንዳትልክልኝ።”
“ድረ ገጹ ላይ ያወጣኸውን ነገር አጥፋ።”
“እንዲህ ማድረግህን ካላቆምክ ሌላ እርምጃ እወስዳለሁ።”
በራስ የመተማመን ስሜትህን አዳብር። በድክመቶችህ ላይ ሳይሆን በጠንካራ ጎኖችህ ላይ ትኩረት አድርግ። (2 ቆሮንቶስ 11:6) አካላዊ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ጉልበተኞች ሁሉ በኢንተርኔት አማካኝነት ጥቃት የሚሰነዝሩ ሰዎችም ዒላማ የሚያደርጉት ደካማ የሚመስሉ ሰዎችን ነው።
ለአንድ ትልቅ ሰው ተናገር። ለወላጆችህ በመናገር መጀመር ትችላለህ። በተጨማሪም ጥቃት የሚሰነዝርብህ ሰው ለሚጠቀመው ድረ ገጽ ወይም የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ ጉዳዩን ሪፖርት ማድረግ ትችላለህ። ሁኔታው በጣም ከተባባሰ ደግሞ ከወላጆችህ ጋር ሆነህ ሁኔታውን ለትምህርት ቤትህ ሪፖርት ማድረግ፣ ለፖሊስ ማሳወቅ ወይም ሕጋዊ እርዳታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ትችላለህ።
ዋናው ነጥብ፦ የሚደርስብህን ጥቃት ለማስቆም ወይም ቢያንስ ጥቃቱ የሚያስከትልብህን ጉዳት ለመቀነስ ልትወስድ የምትችላቸው እርምጃዎች አሉ።