የወጣቶች ጥያቄ
ወላጆቼ በግል ሕይወቴ ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
ወላጆች በልጆቻቸው የግል ሕይወት ውስጥ የሚገቡት ለምንድን ነው?
ወላጆችህ፣ ይህን የሚያደርጉት ስለሚያስቡልህ እንደሆነ ይናገራሉ። አንተ ግን ከልክ በላይ የግል ሕይወትህን ለመቆጣጠር እየሞከሩ እንዳሉ ይሰማሃል። ለምሳሌ ያህል፦
ኤሪን የተባለች የ17 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አባቴ ስልኬን ይወስድና የይለፍ ቃሉን እንድነግረው ይጠይቀኛል፤ ከዚያም የጽሑፍ መልእክቶቼን በሙሉ ያነባል። ለመከልከል ከሞከርኩ ደግሞ የሆነ የምደብቀው ነገር ያለ ይመስለዋል።”
በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ዴኒዝ፣ እናቷ የስልክ ሒሳብ ደረሰኙን ትመረምር እንደነበር ትናገራለች። “የተደዋወልኳቸውን ቁጥሮች አንድ በአንድ እያየች የማን ስልክ ቁጥር እንደሆነ እንዲሁም ከዚያ ሰው ጋር ስለ ምን እንዳወራሁ ትጠይቀኝ ነበር።”
ኬላ የተባለች የ19 ዓመት ወጣትም በአንድ ወቅት እናቷ፣ የግል ጉዳዮቿን የምትጽፍበትን ማስታወሻ እንዳነበበችባት ተናግራለች። “የሚሰማኝን ስሜቴ በተመለከተ የጻፍኳቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ፤ ሌላው ቀርቶ ስለ እሷም ጭምር የጻፍኳቸው አንዳንድ ነገሮች ነበሩ! ከዚያ በኋላ የግል ማስታወሻ መጻፍ አቆምኩ።”
ዋናው ነጥብ፦ ወላጆችህ የአንተን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው፤ ይህን ኃላፊነታቸውን የሚወጡበትን መንገድ በተመለከተ ደግሞ ገደብ ማውጣት አትችልም። እንደሚያበዙት ይሰማሃል? እንደዚያ ሊሰማህ ይችላል። ደስ የሚለው ግን ወላጆችህ ከልክ በላይ መፈናፈኛ እንዳሳጡህ እንዳይሰማህ ማድረግ የምትችልበት መንገድ አለ።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ግልጽ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በሁሉም ነገር በሐቀኝነት እንድንኖር’ ይመክረናል። (ዕብራውያን 13:18) አንተም ከወላጆችህ ጋር በምትነጋገርበት ጊዜ ሐቀኛ ለመሆን ሞክር። ለወላጆችህ ይበልጥ ግልጽና ሐቀኛ በሆንክ መጠን እነሱም ተጨማሪ ነፃነት እየሰጡህ ይሄዳሉ።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ እምነት የሚጣልብህ በመሆን ረገድ ምን ዓይነት ስም አትርፈሃል? በተባልክበት ሰዓት ቤት ትገባለህ? የጓደኞችህን ማንነት ለወላጆችህ ትናገራለህ? የት እንደምትሄድና ምን እንደምታደርግ ለወላጆችህ ታሳውቃለህ?
“ወላጆቼ የምፈልገውን ነገር እንዲያደርጉልኝ ከፈለግኩ እኔም እነሱ የሚፈልጉትን ነገር ማድረግ ይኖርብኛል። በሕይወቴ ውስጥ ስለሚያጋጥሙኝ ነገሮች በግልጽ እነግራቸዋለሁ። ማወቅ የሚፈልጉት ነገር ካለ ምንም ሳልደብቅ እነግራቸዋለሁ፤ ይህ ደግሞ እምነት እንዲጥሉብኝ ስለሚያደርግ ከልክ በላይ በግል ሕይወቴ ውስጥ አይገቡም።”—ዴልያ
ትዕግሥተኛ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም ምግባር ይኑራችሁ” ይላል። (1 ጴጥሮስ 2:12) አልፎ አልፎ ብቻ መልካም ምግባር በማሳየት እምነት የሚጣልብህ እንደሆንክ ማስመሥከር አትችልም፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም መልካም ምግባር ሊኖርህ ይገባል። የወላጆችህን አመኔታ ማትረፍ ጊዜ የሚጠይቅ ነገር ቢሆንም እንዲህ በማድረግህ ፈጽሞ አትቆጭም።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ወላጆችህም በአንድ ወቅት ወጣቶች ነበሩ። ይህ አንተን በሚቆጣጠሩበት መንገድ ላይ ምን ተጽዕኖ የሚያሳድር ይመስልሃል?
“ወላጆች ወጣት በነበሩበት ጊዜ የሠሯቸውን ስህተቶች ስለሚያስታውሱ ልጆቻቸውም ያንኑ ስህተት እንዳይደግሙ የሚፈሩ ይመስለኛል።”—ዳንኤል
የወላጆችህን ስሜት ለመረዳት ሞክር። ጉዳዩን በወላጆችህ ቦታ ሆነህ ለማሰብ ሞክር። መጽሐፍ ቅዱስ ባለሙያ ሚስት ‘የቤተሰቧን እንቅስቃሴ በደንብ እንደምትከታተል’ እንዲሁም ጥሩ አባት ልጆቹን ‘በይሖዋ ተግሣጽና መመሪያ እንደሚያሳድግ’ ይናገራል። (ምሳሌ 31:27፤ ኤፌሶን 6:4 የግርጌ ማስታወሻ) ይህን ለማድረግ ደግሞ ወላጆችህ የግድ ስለ ግል ሕይወትህ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶችን በተመለከተ የምታውቃቸውን ነገሮች እስቲ ለማሰብ ሞክር፤ አንተ ወላጅ ብትሆን ኖሮ በልጅህ ሕይወት ውስጥ ምንም ጣልቃ ሳትገባ በግል ሕይወቱ ላይ ሙሉ ነፃነት እንዲኖረው ትፈቅድ ነበር?
“በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለሁ ወላጆቼ የግል ሕይወቴን እንደማያከብሩልኝ ይሰማኝ ነበር። ከፍ እያልኩ ስሄድ ግን ወላጆቼ እንደዚያ ያደረጉበት ምክንያት እየገባኝ መጣ። እንዲህ የሚያደርጉት ስለሚወዱኝ ነው።”—ጄምስ