የወጣቶች ጥያቄ
አሉታዊ አመለካከትን ማስወገድ የምችለው እንዴት ነው?
ምን ዓይነት ሰው ነህ?
አዎንታዊ
“በተቻለኝ መጠን ደስተኛ ለመሆንና በቀላሉ ላለመበሳጨት እሞክራለሁ። ፈገግታ ሁሌም ከፊቴ ባይለይ ደስ ይለኛል።”—ቫለሪ
አሉታዊ
“ጥሩ ነገር ስሰማ ወዲያው የሚቀናኝ ‘ሊሆን አይችልም’ ወይም ‘የሆነ ችግር አለበት’ ብሎ ማሰብ ነው።”—ሬቤካ
ሚዛናዊ
“ሁልጊዜ አዎንታዊ መሆን ለብስጭት ሊዳርግ ይችላል፤ አሉታዊ መሆን ደግሞ መቼም ደስታ አያስገኝም። ሚዛናዊ መሆኔ ነገሮችን በምክንያታዊነት ለማየት ረድቶኛል።”—አና
ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?
መጽሐፍ ቅዱስ “ደስተኛ ልብ ያለው ሰው . . . ሁልጊዜ ግብዣ ላይ ያለ ያህል ነው” ይላል። (ምሳሌ 15:15) አሉታዊ በሆኑ ሐሳቦች ራሳቸውን ከማስጨነቅ ይልቅ አዎንታዊ አመለካከት ይዘው ሕይወታቸውን የሚመሩ ሰዎች ደስተኛ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። እንዲህ ያሉ ሰዎች ጓደኛ ማግኘት ይቀላቸዋል። ደግሞስ ሁሌ ከሚያማርር ሰው ጋር ጓደኛ መሆን የሚፈልግ ማን አለ?
ያም ቢሆን አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎችም ሊጋፈጧቸው የሚገቡ አሳዛኝ እውነታዎች አሉ። ለምሳሌ፦
በዜና ማሰራጫዎች ላይ ስለ ጦርነት፣ ስለ ሽብርተኝነትና ስለ ወንጀል በየቀኑ መስማትህ አይቀርም።
በቤተሰብህ ውስጥ ችግር ሊያጋጥምህ ይችላል።
ከግል ድክመቶችህ ጋር መታገል እንደሚያስፈልግህ ጥያቄ የለውም።
ጓደኞችህ ስሜትህን ሊጎዱት ይችላሉ።
እንዲህ ያሉትን ችግሮች በቸልታ ከማለፍ ወይም በችግሩ ላይ ከመጠን በላይ ከመብሰልሰል ይልቅ ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት አድርግ። ሚዛናዊ መሆንህ አሉታዊ በሆኑ ሐሳቦች ከመጠን በላይ እንዳትጠመድና ችግሮች ሲያጋጥሙህ ተስፋ እንዳትቆርጥ ይረዳሃል።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ለስህተቶችህ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ።
መጽሐፍ ቅዱስ “ሁልጊዜ ጥሩ ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኃጢአት የማይሠራ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም” ይላል። (መክብብ 7:20) ስህተት መሥራትህ ሰው መሆንህን እንጂ ዋጋ ቢስ መሆንህን የሚያሳይ አይደለም።
ሚዛናዊ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ስህተትህን ለማረም ጥረት አድርግ፤ ሆኖም ከራስህ ፍጽምና አትጠብቅ። ካሌብ የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “በስህተቶቼ ላይ ትኩረት ላለማድረግ እሞክራለሁ። ከዚህ ይልቅ ማሻሻያ ማድረግ እንድችል ከስህተቶቼ ለመማር ጥረት አደርጋለሁ።”
ራስህን ከሌሎች ጋር አታወዳድር።
መጽሐፍ ቅዱስ “በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ” ይላል። (ገላትያ 5:26) አንተ ባልተጋበዝክባቸው ግብዣዎች ላይ ጓደኞችህ የተነሷቸውን ፎቶዎች ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ብታይ ልታዝን ትችላለህ። ይህም ከጓደኞችህ ጋር ያለህ ወዳጅነት እንዲሻክር ሊያደርግ ይችላል።
ሚዛናዊ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? በሁሉም ግብዣዎች ላይ ልትጠራ እንደማትችል አምነህ ተቀበል። በዚያ ላይ ደግሞ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የወጣው ፎቶ የተሟላ መረጃ የያዘ ላይሆን ይችላል። አሌክሲስ የተባለች ወጣት “ሰዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያወጡት ያጋጠማቸውን አስደሳች ነገር ብቻ ነው። ሌላውን ነገር ግን ያስቀሩታል” ብላለች።
በተለይ በቤተሰብህ ውስጥ ሰላም ፈጣሪ ሁን።
መጽሐፍ ቅዱስ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ” ይላል። (ሮም 12:18) ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባትችልም የምትሰጠውን ምላሽ መቆጣጠር ግን ትችላለህ። ሰላማዊ መሆን ትችላለህ።
ሚዛናዊ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ከጓደኞችህ ጋር እንደምታደርገው ሁሉ ከቤተሰብህ አባላት ጋር ስትሆንም ግንኙነታችሁን የሚያሻክር ነገር ላለማድረግ ከዚህ ይልቅ ሰላማዊ ለመሆን ጥረት አድርግ። ሜሊንዳ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ፍጹም ሰው የለም። ስለዚህ አንዳችን ሌላውን የሚያበሳጭ ነገር ማድረጋችን አይቀርም። እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥመን ሰላማዊ ለመሆን መጣር ይኖርብናል።”
አመስጋኝ ሁን።
መጽሐፍ ቅዱስ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ” ይላል። (ቆላስይስ 3:15) አመስጋኝ መሆንህ በሕይወትህ ውስጥ ባሉት ችግሮች ላይ ሳይሆን ባሉህ ጥሩ ነገሮች ላይ ለማተኮር ይረዳሃል።
ሚዛናዊ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ችግሮች እንዳሉብህ አምነህ ተቀበል፤ ሆኖም በሕይወትህ የሚያጋጥሙህን መልካም ነገሮችም አትርሳ። ሬቤካ የተባለች ወጣት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “በየቀኑ ያገኘሁትን አንድ ጥሩ ነገር የመጻፍ ልማድ አለኝ። በጥቅሉ ሲታይ ሕይወቴ በመልካም ነገሮች የተሞላ እንደሆነ ለማሰብ እሞክራለሁ።”
ጥሩ ጓደኞች ምረጥ።
መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ጓደኞችህ ተቺ፣ አጉረምራሚ ወይም ሁልጊዜ የሚያማርሩ ከሆኑ እንዲህ ያሉት አሉታዊ ባሕርያት ሊጋቡብህ ይችላሉ።
ሚዛናዊ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ጓደኞችህ ችግር ሲያጋጥማቸው ለተወሰነ ጊዜ አሉታዊ አመለካከት ሊያድርባቸው ይችላል። በዚህ ጊዜ ድጋፍ ልታደርግላቸው ይገባል፤ ሆኖም የእነሱ ችግር በአሉታዊ ስሜት እንድትዋጥ ሊያደርግህ አይገባም። ሚሼል የተባለች ወጣት “ጓደኞቻችን በሙሉ አሉታዊ ሰዎች ሊሆኑ አይገባም” ብላለች።
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት
የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ብሎ በሚጠራው ዘመን ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ብዙ አሉታዊ ነገሮች ባሉበት ዓለም ውስጥ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ከባድ እንደሆነ ይሰማሃል? “መከራ የበዛው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።