የወጣቶች ጥያቄ
ወላጆቼ ቢፋቱስ?
በአንድ ወጣት ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ጭንቀት ሊፈጥሩ ከሚችሉ ሁኔታዎች አንዱ የወላጆች ፍቺ ነው። ታዲያ ሐዘኑን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?
በዚህ ርዕስ ውስጥ
ልታደርጋቸው የማይገቡ ሦስት ነገሮች
1. ራስህን ተጠያቂ ማድረግ
“እናቴ በእሷና በአባቴ መካከል ችግሮች መፈጠር የጀመሩት እኔ ስወለድ እንደሆነ ነግራኝ ነበር። ስለዚህ ለወላጆቼ ትዳር መፍረስ መንስኤው እኔ እንደሆንኩ ማሰብ ጀመርኩ።”—ዳያና
ይህን አስታውስ፦ ፍቺው ከአንተ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ አይደለም። በወላጆችህ መካከል ያለ ነገር ነው። የችግራቸው መንስኤ አንተ አይደለህም፤ መፍትሔው ያለውም በአንተ እጅ አይደለም። በትዳራቸው ውስጥ የተፈጠረውን ችግር መፍታት አለመፍታት የእነሱ ድርሻ ነው።
2. ቂም መያዝ
“አባቴ ለእናቴ ታማኝ አለመሆኑ በጣም አበሳጭቶኛል። ከዚህ በኋላ እሱን ማመን በጣም ይከብደኛል።”—ሪአና
ይህን አስታውስ፦ በወላጆችህ መካከል የተፈጠረው ነገር ቢያስቆጣህ ወይም ቅር ቢያሰኝህ የሚጠበቅ ነገር ነው። እየተበሳጩ መኖር ግን ጤናማ አይደለም። የአንተን አካላዊና አእምሯዊ ጤንነት ሊጎዳው ይችላል። ብዙ ጊዜ እንደሚባለው ቂም መያዝ፣ መርዝ ጠጥቶ ሌላኛው ሰው እንዲጎዳ እንደመጠበቅ ነው። a
3. አንተም ብታገባ ተመሳሳይ ዕጣ እንደሚጠብቅህ ማሰብ
“የአባቴ ዓይነት ሰው ቢወጣኝስ ብዬ በጣም እፈራለሁ። አንድ ቀን አግብቼ ልጆች ብወልድ፣ የወላጆቼ ትዳር ወደ ፍቺ እንዲያመራ ያደረገውን ነገር አድርጌ ልገኝ እንደምችል በማሰብ እጨነቃለሁ።”—ጄሲካ
ይህን አስታውስ፦ የወላጆችህ ትዳር በፍቺ ስለፈረሰ ብቻ የአንተም ትዳር ተመሳሳይ ዕጣ ይገጥመዋል ማለት አይደለም። እንዲያውም ከወላጆችህ ገጠመኝ ጠቃሚ ትምህርቶች ማግኘት ትችላለህ። ለምሳሌ፣ ትዳር ስታስብ ከትዳር ጓደኛህ በምትጠብቃቸው ባሕርያት ረገድ ይበልጥ ንቁ ትሆናለህ። በሌላ በኩል ደግሞ አንተ ራስህ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ለመሆን የሚረዱህን ባሕርያት ለማዳበር ቆርጠህ ትነሳለህ።
ልታደርጋቸው የምትችላቸው ሦስት ነገሮች
1. ሐሳብህን ግለጽ። አሉታዊ ስሜቶችን አፍነው ለመያዝ የሚሞክሩ ሰዎች ለጎጂ ልማዶች ሊጋለጡ ይችላሉ፤ ለምሳሌ ከመጠን በላይ መጠጣት ወይም ዕፅ መውሰድ። አንተም በዚህ ጎዳና ከመሄድ ይልቅ እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦
ወላጆችህን አነጋግር። አንደኛው ወይም ሁለቱም ወላጆችህ በራሳቸው ችግር አንተን ሊያስገቡህ እየሞከሩ ከሆነ ይህ ስለሚፈጥርብህ ስሜት በተረጋጋ መንፈስ ሆኖም በግልጽ ንገራቸው። በአካል ማነጋገር ከከበደህ ለአንዳቸው ወይም ለሁለቱም ደብዳቤ መጻፍ ትችላለህ።
የምታምነውን ጓደኛህን አነጋግር። ጆሮ ሰጥቶ የሚሰማህ ሰው መኖሩ በራሱ ትልቅ እፎይታ እንዲሰማህ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው” ይላል።—ምሳሌ 17:17
ፈጣሪህን አነጋግር። “ጸሎት ሰሚ” የሆነው ይሖዋ በፈለግኸው ሰዓት ይሰማሃል። (መዝሙር 65:2) መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል” ይላል።—1 ጴጥሮስ 5:7
ረጋ እና ሰከን ብለህ ለማነጋገር የሚቀልህ የትኛው ወላጅህ ነው? አባትህ ወይስ እናትህ?
ከጎንህ ሆኖ እንዲያግዝህ የትኛውን ወዳጅህን ማነጋገር ትችላለህ? (እኩያህ ወይም በዕድሜ የሚበልጥህ ሊሆን ይችላል)
ስለ የትኞቹ ጉዳዮች መጸለይ ትችላለህ?
2. ለውጥን እንደ አመጣጡ አስተናግድ
ወላጆችህ በመፋታታቸው ምክንያት ቤትህ፣ ትምህርት ቤትህ ወይም የገቢያችሁ መጠን ሊቀየር ይችላል፤ ሌላው ቀርቶ አዳዲስ ጓደኞች ማፍራት ሊኖርብህ ይችላል። እነዚህ ለውጦች ቢያስከፉህ ወይም ውጥረት ቢፈጥሩብህ የሚያስገርም አይደለም፤ ሕይወትህ ምስቅልቅሉ እንደወጣ ሊሰማህ ይችላል። ታዲያ ለውጡን ማስተናገድ ቀላል እንዲሆንልህ የሚያደርገው ምንድን ነው? አዲሱን ሁኔታ ለመላመድ ማድረግ በምትችለው ነገር ላይ ማተኮር ነው።
በወላጆችህ ፍቺ የተነሳ የገጠመህ ትልቁ ለውጥ ምንድን ነው?
ይህን ለውጥ ለመልመድ ምን እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ?
3. ጠንካራ ጎንህን ለይተህ እወቅ
ወላጆችህ መፋታታቸው በጣም ሊያስጨንቅህ ቢችልም የራስህን ጥንካሬ ማወቅ የምትችልበት አጋጣሚም ይሰጥሃል። ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል ያልነበሩህን ተፈላጊ ባሕርያት ለማዳበርም ሊረዳህ ይችላል። በ13 ዓመቱ ወላጆቹ የተፋቱበት ጀረሚ እንዲህ ብሏል፦ “የወላጆቼ ፍቺ፣ ይበልጥ ኃላፊነት የሚሰማኝ ሰው እንድሆን አድርጎኛል። የቤቱ ትልቅ ልጅ እኔ እንደመሆኔ መጠን እናቴን ይበልጥ ማገዝ እንዲሁም ታናሽ ወንድሜን መርዳት ነበረብኝ።”
በወላጆችህ መካከል የተፈጠረው ችግር የትኞቹን ጠንካራ ጎኖችህን እንድታስተውል አድርጎሃል?
የትኞቹ ባሕርያት ላይ መሥራት ትፈልጋለህ?
a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ቁጣዬን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።