የወጣቶች ጥያቄ
የመንፈስ ጭንቀትን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
የመንፈስ ጭንቀትን ለመቋቋም የሚያስችል ጥሩ ዕቅድ ካወጣህ የሚሰማህ ጭንቀት በእጅጉ ሊቀልልህ ይችላል!
አንተ ብትሆን ምን ታደርጋለህ?
እስቲ የሚከተሉትን ሁኔታዎች በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር፦
ጄኒፈር ምንም የሚያስደስታት ነገር የለም። ያለ ምንም ምክንያት በየዕለቱ ታለቅሳለች። ራሷን ከሰዎች ታገላለች፤ እንዲሁም ምግብ አይበላላትም። እንቅልፍ የማይወስዳት ከመሆኑም በላይ በአንድ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ አትችልም። ጄኒፈር ‘ምን እየሆንኩ ነው? እንደ በፊቱ ዓይነት ሕይወት ይኖረኝ ይሆን?’ ብላ ታስባለች።
ማርክ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነበር። አሁን ግን ትምህርት ቤት መሄድ ራሱ ያስጠላዋል፤ ውጤቱም እያሽቆለቆለ ነው። በፊት ይወዳቸው የነበሩትን ጨዋታዎች ለመጫወት እንኳ አቅም የለውም። ጓደኞቹ ግራ ተጋብተዋል። ወላጆቹም በጣም ተጨንቀዋል። ታዲያ ይህ በራሱ የሚያልፍ ነገር ነው ወይስ ከባድ ችግር?
አንተስ እንደ ጄኒፈር ወይም እንደ ማርክ ዓይነት ስሜት ይሰማሃል? ከሆነ፣ ምን ማድረግ ትችላለህ? እነዚህን ሁለት አማራጮች መሞከር ትችል ይሆናል፦
ሀ. ችግሩን በራስህ ለመቋቋም መሞከር
ለ. ችግሩን ለአንድ የምታምነው ትልቅ ሰው መናገር
ከሰው ጋር መነጋገር የማያስደስትህ ከሆነ ምርጫ ሀ የተሻለ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ግን ይህ የተሻለው ምርጫ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል . . . አንዱ ቢወድቅ ሁለተኛው ባልንጀራውን ደግፎ ሊያነሳው ይችላልና። ይሁንና ደግፎ የሚያነሳው ሰው በሌለበት አንዱ ቢወድቅ እንዴት ይሆናል?”—መክብብ 4:9, 10
ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ ወንጀል በሚፈጸምበት አንድ አደገኛ ሰፈር ውስጥ ሆነህ መንገድ ጠፋብህ እንበል። አካባቢው ጨለማ ነው፤ ወንጀለኞች ጉዳት ለማድረስ በየቦታው አድፍጠው ይጠብቃሉ። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋለህ? መውጫ መንገዱን ራስህ ፈልገህ ለማግኘት ትሞክር ይሆናል። ሆኖም፣ አንድ የምታምነው ሰው ጋር ደውለህ እንዲረዳህ ብትጠይቀው የተሻለ አይሆንም?
የመንፈስ ጭንቀት ልክ እንደዚያ አደገኛ ሰፈር ነው። እርግጥ ነው፣ ጊዜያዊ የሆነ የድብርት ስሜት ጊዜ ሲያልፍ በራሱ ይጠፋ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ያለው ስሜት ለረጅም ጊዜ ከቀጠለ እርዳታ መጠየቁ የተሻለ ይሆናል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ‘ራሱን የሚያገል ሰው ሁሉ ጥበብን ሁሉ ይቃወማል።’—ምሳሌ 18:1
ምርጫ ለ ግን ጥቅም አለው፤ ለወላጅህ ወይም ለምታምነው ሌላ ትልቅ ሰው ችግርህን መናገርህ ቀደም ሲል እንዲህ ያሉ ስሜቶችን ተቋቁሞ ያለፈ ሰው ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት ከሚሰጥህ ምክር ጥቅም እንድታገኝ ይረዳሃል።
‘ወላጆቼ እንዲህ ስላለው ስሜት ምንም የሚያውቁት ነገር የለም!’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ሆኖም ይህን በእርግጠኝነት መናገር ትችላለህ? እነሱ ወጣት በነበሩበት ወቅት ያጋጥሟቸው ሁኔታዎች አንተን ካጋጠሙህ የተለዩ ቢሆኑም እንኳ ይሰማቸው የነበረው ስሜት ግን ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ከችግርህ የምትገላገልበት መፍትሔ ይጠቁሙህ ይሆናል!
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በዕድሜ በገፉት መካከል ጥበብ፣ ከረጅም ዕድሜስ ጋር ማስተዋል አይገኝም?”—ኢዮብ 12:12
ዋናው ነጥብ፦ ለወላጆችህ ወይም ለምታምነው ሌላ ትልቅ ሰው ችግርህን መናገርህ ጥሩ የመፍትሔ ሐሳብ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል።
የሕክምና እርዳታ ማግኘት ያስፈልግ ይሆን?
በየቀኑ በጭንቀት የምትዋጥ ከሆነ፣ ይህ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልገው ከባድ የመንፈስ ጭንቀት እንዳለብህ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።
ከባድ የመንፈስ ጭንቀት የያዛቸው በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ወጣቶች የሚታይባቸው ምልክት ታዳጊ ወጣቶች ከሚያጋጥማቸው የተለመደ የስሜት መለዋወጥ ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም የጭንቀት ስሜቱ ይበልጥ ከባድና ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ይሆናል። በመሆኑም የሚሰማህ የሐዘን ስሜት ከባድና ለረጅም ጊዜ የሚቀጥል ከሆነ ከወላጆህ ጋር በመነጋገር ለምን የሕክምና ምርመራ አታደርግም?
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም።”—ማቴዎስ 9:12
የምርመራው ውጤት ከባድ የመንፈስ ጭንቀት እንዳለብህ የሚያሳይ ቢሆን እንኳ ምንም የሚያሳፍር ነገር የለውም። ብዙ ወጣቶች የመንፈስ ጭንቀት ያጋጥማቸዋል፤ በተጨማሪም ሊድን የሚችል ነገር ነው። እውነተኛ ጓደኞችህ በዚህ ምክንያት ለአንተ ያላቸው ግምት አይቀንስም።
ጠቃሚ ምክር፦ ትዕግሥተኛ ሁን። ከመንፈስ ጭንቀት መላቀቅ ጊዜ የሚወስድ ነገር ነው፤ እንዲሁም ችግሩ ቀለል የሚልበት እና የሚከብድበት ጊዜ እንዳለ ማወቅ አለብህ። a
ስሜትህን ለማስተካከል የሚረዱ ዘዴዎች
የሕክምና እርዳታ ማግኘት የሚያስፈልግህ ሆነም አልሆነ የሚሰማህን ከባድ ሐዘን ለመቋቋም ማድረግ የምትችላቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አዘውትሮ ስፖርት መሥራት፣ ጤናማ የአመጋገብ ልማድ ማዳበር፣ እንዲሁም በቂ እንቅልፍ ማግኘት ስሜትህን ለማስተካከል ሊረዱህ ይችላሉ። (መክብብ 4:6፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:8) እንዲሁም የሚሰማህን ስሜት፣ ስሜትህን ለማስተካከል የሚረዱህን እርምጃዎች፣ የሚያጋጥሙህን እንቅፋቶችና ያገኘሃቸውን ስኬቶች የምትጽፍበት ማስታወሻ እንዲኖርህ ማድረጉ ይረዳህ ይሆናል።
የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልገው ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ቢኖርብህም ሆነ ጊዜያዊ የሆነ መጥፎ ስሜት እየተሰማህ ቢሆን፣ ይህን ማስታወስህ አስፈላጊ ነው፦ ሌሎች ሰዎች የሚሰጡህን እርዳታ ከተቀበልክና ስሜትህን ለማስተካከል የሚረዱ እርምጃዎችን ከወሰድክ የመንፈስ ጭንቀትን መቋቋም ትችላለህ።
ሊረዱህ የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች
“ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውንም ያድናል።”—መዝሙር 34:18
“ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል። ጻድቁ እንዲወድቅ ፈጽሞ አይፈቅድም።”—መዝሙር 55:22
“‘አትፍራ። እረዳሃለሁ’ የምልህ እኔ፣ አምላክህ ይሖዋ ቀኝ እጅህን ይዣለሁና።”—ኢሳይያስ 41:13
“ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ።”—ማቴዎስ 6:34
“ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
a ሕይወትህን የማጥፋት ሐሳብ ከመጣብህ፣ ወዲያውኑ ከአንድ የምታምነው ትልቅ ሰው እርዳታ ጠይቅ። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሚያዝያ 2014 ንቁ! ላይ የወጣውን “መኖር ምን ዋጋ አለው?” የሚል አራት ተከታታይ ክፍል ያለው ርዕስ ተመልከት።