የወጣቶች ጥያቄ
የጤና ችግር ቢኖርብኝ ምን ላድርግ? (ክፍል 3)
ቭሎሪያ
ፋይብሮማያልጂያ የሚባል በሽታ የያዘኝ ከ14 ዓመቴ ጀምሮ ነው። ሃያ ዓመት ሲሆነኝ ደግሞ በአርትራይተስ፣ በሉፐስና በላይም በሽታ ተጠቃሁ። ሁልጊዜ አቅም ስለሚያንሰኝ ማድረግ የምፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ማድረግ እቸገር ነበር። አንዳንድ ጊዜ ከወገቤ በታች ያለውን የሰውነቴን ክፍል ማንቀሳቀስ ስለማልችል የግድ ተሽከርካሪ ወንበር መጠቀም ያስፈልገኛል።
በሽታው ከሚያስከትልብኝ አካላዊ ሕመም የባሰ ከባድ የነበረው እንደ መጻፍና የተከደኑ ዕቃዎችን እንደ መክፈት ያሉ ቀላል ሥራዎችን ማከናወን ባለመቻሌ ይሰማኝ የነበረው የስሜት ሥቃይ ነበር። ልጆች ሲራመዱ ሳይ ‘እኔ እንደ እነሱ መራመድ ያልቻልኩት ለምንድን ነው?’ ብዬ አስባለሁ። ምንም እንደማልረባ ይሰማኝ ነበር።
ደስ የሚለው ከቤተሰቤ ብቻ ሳይሆን ከምሰበሰብበት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤም ጭምር እርዳታ አግኝቻለሁ። በጉባኤያችን ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች፣ ብዙ ጊዜ እየመጡ ስለሚጠይቁኝ ያን ያህል የብቸኝነት ስሜት አይሰማኝም። እኔን ከተሽከርካሪ ወንበሬ ላይ ማውረድ እንዲሁም መኪና ውስጥ ማስገባትና ማስወጣት ቀላል ባይሆንም እንኳ አንዳንዶች ሲሰባሰቡ አብሬያቸው እንድገኝ ይጋብዙኝ ነበር።
በተለይ በጉባኤያችን ያሉ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች የጤና ችግር ምን ስሜት እንደሚያሳድር ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ትልቅ እርዳታ አበርክተውልኛል። የአቅም ገደብ እንዳለብኝ አምኜ እንድቀበልና ሌሎች ከሚያደርጉት እኩል ማድረግ ባለመቻሌ የጥፋተኝነት ስሜት እንዳይሰማኝ ረድተውኛል። ከምንም በላይ የሚያስደስተኝ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና በአገልግሎት መካፈል ነው። (ዕብራውያን 10:25) የጤና ችግር ቢኖርብኝም እንኳ በእነዚህ ወቅቶች ከሌሎች ሰዎች ብዙም የተለየሁ እንዳልሆንኩ እረዳለሁ።
ይሖዋ ለመጽናት የሚያስፈልገንን ብርታት እንደሚሰጠን ሁልጊዜ ለማስታወስ እጥራለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ውጫዊው ሰውነቱ እየመነመነ ቢሄድም ውስጣዊው ሰውነቱ “ከቀን ወደ ቀን እየታደሰ” ሊሄድ እንደሚችል ይናገራል። (2 ቆሮንቶስ 4:16) እኔም ልክ እንደዚህ ይሰማኛል!
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ በከባድ የጤና ችግር እየተሠቃየህ ከሆነ፣ ከሌሎች ጋር መቀራረብህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ጤናማ ከሆንክ ደግሞ፣ አንድን የታመመ ሰው መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?—ምሳሌ 17:17
ጀስቲን
መሬት ላይ ከወደቅኩ በኋላ መነሳት አቃተኝ። ደረቴ ላይ ጭንቅ ስላለኝ መንቀሳቀስ አልቻልኩም። ከዚያም በፍጥነት ወደ ድንገተኛ ክፍል ተወሰድኩ። መጀመሪያ ላይ ዶክተሮቹ በሽታዬን ማወቅ አልቻሉም ነበር። በተደጋጋሚ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመኝ በኋላ ግን ላይም የተባለ በሽታ እንደያዘኝ አወቁ።
ይህ በሽታ በሰውነቴ የነርቭ ሥርዓት ላይ ጉዳት አድርሷል። በዚህ በሽታ እንደተያዝኩ ከታወቀ በርካታ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም አሁንም ድረስ ሰውነቴ የሚንቀጠቀጥ ሲሆን አንዳንዴ ከቁጥጥሬ ውጭ ይሆናል። አንዳንድ ቀን መላ ሰውነቴን በጣም ያመኛል፤ ወይም ደግሞ ጣቶቼን በጣም ስለሚያመኝ ማንቀሳቀስ እንኳ ያቅተኛል። መገጣጠሚያዎቼ ሁሉ እንደዛጉ ሆኖ ይሰማኛል።
‘በዚህ ዕድሜዬ እኮ ይህን ያህል መታመም አልነበረብኝም’ ብዬ አስብ የነበረ ሲሆን ይህም እንድበሳጭ ያደርገኛል። በየዕለቱ “ይህ ሁሉ ሥቃይ እየደረሰብኝ ያለው ለምንድን ነው?” እያልኩ ወደ አምላክ እጮኽ ነበር። እንዲያውም አምላክ ጨርሶ እንደተወኝ ይሰማኝ ጀመር። ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ኢዮብ ትዝ አለኝ። ኢዮብ ያ ሁሉ ሥቃይ እየደረሰበት ያለው ለምን እንደሆነ ባያውቅም ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። ኢዮብ ያን ያህል ከባድ ችግር እየደረሰበትም ታማኝ መሆን ከቻለ፣ እኔም እንደ እሱ ማድረግ አያቅተኝም።
የጉባኤዬ ሽማግሌዎች ትልቅ እርዳታ አድርገውልኛል። ስለ ደህንነቴ ሁልጊዜ ይጠይቁኛል። እንዲያውም አንድ ሽማግሌ ላናግረው የምፈልገው ነገር ካለ በማንኛውም ሰዓት ልደውልለት እንደምችል ነገረኝ። ይሖዋ እነዚህን የመሰሉ ወዳጆች ስለሰጠኝ በየዕለቱ አመሰግነዋለሁ።—ኢሳይያስ 32:1, 2
አንዳንድ ጊዜ ከባድ ሕመም ሲያጋጥመን ግልጽ የሆነውን እውነታ ይኸውም ይሖዋ እየደረሰብን ያለውን ሥቃይ እንደሚረዳ እንዘነጋለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል” ይላል። (መዝሙር 55:22) እኔም በየቀኑ ይህን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እሞክራለሁ።
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የሌሎች ሰዎች እርዳታ፣ ያጋጠመህን የጤና ችግር እንድትቋቋም የሚረዳህ እንዴት ነው?—ምሳሌ 24:10፤ 1 ተሰሎንቄ 5:11
ኒሳ
በአሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ሳለሁ ማርፋን ሲንድሮም በመባል የሚታወቅ መገጣጠሚያን የሚያጠቃና አቅም የሚያሳጣ በሽታ እንዳለብኝ አወቅኩ። ይህ በሽታ በልብ፣ በዓይን እንዲሁም በሌሎች ዋና ዋና የሰውነት ክፍሎች ላይም ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። በየቀኑ ሕመም የሚሰማኝ ባይሆንም እንኳ ሕመሙ ሲጀምረኝ ግን በጣም ያሠቃየኛል።
ይህ በሽታ እንዳለብኝ ሲነገረኝ በጣም አለቀስኩ። የሚያስደስቱኝን ነገሮች ማድረግ አለመቻሌ አስጨነቀኝ። ለምሳሌ ያህል፣ መደነስ በጣም እወዳለሁ፤ ሆኖም ወደፊት፣ መደነስ ቀርቶ መራመድ እንኳ በጣም ሊከብደኝ እንደሚችል ሳስብ ፍርሃት አደረብኝ።
እህቴ ትልቅ ድጋፍ ሆናኛለች። ስለ ራሴ እያሰብኩ ከመቆዘም እንድላቀቅ ረድታኛለች። ፍርሃት ኃይሌን ስለሚያሟጥጠው በፍርሃት መኖር እንደሌለብኝ ነገረችኝ። እንዲሁም ከማንም በላይ ሁኔታዬን የሚረዳው ይሖዋ በመሆኑ ያለማቋረጥ ወደ እሱ እንድጸልይ አበረታታችኝ።—1 ጴጥሮስ 5:7
በጣም የሚያበረታታኝ ጥቅስ መዝሙር 18:6 ነው። እንዲህ ይላል፦ “በጭንቅ ውስጥ ሳለሁ ይሖዋን ጠራሁት፤ እርዳታ ለማግኘት አምላኬን አጥብቄ ተማጸንኩት። በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ፤ እርዳታ ለማግኘት የማሰማውም ጩኸት ወደ ጆሮው ደረሰ።” ይህ ጥቅስ ይሖዋ በሽታዬን ለመቋቋም እንዲረዳኝ የማቀርበውን ልመና እንደሚሰማኝና እንደሚረዳኝ እንድገነዘብ አስችሎኛል። ይሖዋ ምንጊዜም ከጎኔ አይለይም።
መጥፎ ነገር ሲደርስብን ማዘንና መከፋት በራሱ ስህተት እንዳልሆነ ተምሬአለሁ፤ ሆኖም የሚሰማን ስሜት ኃይላችንን እንዲያሟጥጠውና ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት እንዲነካው መፍቀድ አይኖርብንም። የችግሮቻችን መንስኤ አምላክ አይደለም፤ ደግሞም በሕይወታችን ለእሱ ቅድሚያውን እስከሰጠን ድረስ በጭራሽ አይተወንም።—ያዕቆብ 4:8
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ለሚደርስብን ሥቃይ ተጠያቂው አምላክ ነው?—ያዕቆብ 1:13