የወጣቶች ጥያቄ
ልጠመቅ?—ክፍል 1፦ የጥምቀት ትርጉም
በየዓመቱ በይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ በርካታ ወጣቶች ይጠመቃሉ። አንተስ ይህን እርምጃ ለመውሰድ እያሰብክ ነው? ከሆነ በመጀመሪያ ራስን መወሰን እና መጠመቅ ምን ትርጉም እንዳለው መረዳት ይኖርብሃል።
ጥምቀት ምንድን ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ጥምቀት የሚያመለክተው በውኃ መረጨትን ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መጥለቅን ነው፤ ይህ ደግሞ ልዩ ትርጉም አለው።
ስትጠመቅ ውኃ ውስጥ መጥለቅህ ከዚህ በኋላ የምትኖረው ራስህን ለማስደሰት እንዳልሆነ ለሰዎች ያሳያል።
ከውኃው መውጣትህ አምላክን በማስደሰት ላይ ያተኮረ አዲስ ሕይወት መምራት እንደጀመርክ ያሳያል።
መጠመቅህ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ መሥፈርት የማውጣት ሥልጣን ያለው ይሖዋ እንደሆነ አምነህ መቀበልህን በይፋ ያሳያል፤ በተጨማሪም ይሖዋ የሚጠብቅብህን ነገር በፈቃደኝነት ለማድረግ ቃል መግባትህን ለሰዎች ታሳያለህ።
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ይሖዋን በመታዘዝ ላይ ያተኮረ ሕይወት ለመምራት በሕዝብ ፊት ቃል መግባትህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንደኛ ዮሐንስ 4:19ን እና ራእይ 4:11ን ተመልከት።
ራስን መወሰን ምንድን ነው?
ከመጠመቅህ በፊት ብቻህን ሆነህ ራስህን ለይሖዋ መወሰን ይኖርብሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
በግልህ ወደ ይሖዋ ጸሎት በማቅረብ እሱን ለዘላለም ለማገልገል ቃል መግባትህን እንዲሁም ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ ወይም ሌሎች ምንም ቢያደርጉ የእሱን ፈቃድ እንደምታደርግ ትነግረዋለህ።
ጥምቀት ብቻህን ሆነህ ያደረግከውን ይህን ውሳኔ ለሰዎች የምታሳይበት ሥነ ሥርዓት ነው። መጠመቅህ ራስህን መካድህንና ከዚህ በኋላ የይሖዋ ንብረት መሆንህን ለሌሎች ያሳያል።—ማቴዎስ 16:24
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የይሖዋ ንብረት መሆንህ የተሻለ ሕይወት እንድትመራ የሚረዳህ እንዴት ነው? ኢሳይያስ 48:17, 18ን እና ዕብራውያን 11:6ን ተመልከት።
መጠመቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ፣ መጠመቅ ከደቀ መዛሙርቱ የሚጠበቅ ብቃት እንደሆነ ገልጿል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ስለዚህ ዛሬም ጥምቀት ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ብቃት ነው። እንዲያውም ጥምቀት ለመዳን አስፈላጊ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—1 ጴጥሮስ 3:21
ሆኖም ለመጠመቅ የሚያነሳሳህ ለይሖዋ ያለህ ፍቅርና አድናቆት ሊሆን ይገባል። እንደ መዝሙራዊው ዓይነት አመለካከት ሊኖርህ ይገባል፤ መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ላደረገልኝ መልካም ነገር ሁሉ ለይሖዋ ምን እመልስለታለሁ? [የይሖዋን] ስም እጠራለሁ። . . . ስእለቴን ለይሖዋ እፈጽማለሁ።”—መዝሙር 116:12-14
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ይሖዋ ምን መልካም ነገር አድርጎልሃል? ምን ልትመልስለትስ ትችላለህ? ዘዳግም 10:12, 13ን እና ሮም 12:1ን ተመልከት።