በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የፍቅር ጓደኝነት—ክፍል 1፦ የፍቅር ጓደኛ ለመያዝ ደርሻለሁ?

የፍቅር ጓደኝነት—ክፍል 1፦ የፍቅር ጓደኛ ለመያዝ ደርሻለሁ?

የፍቅር ጓደኝነት ምንድን ነው?

  አንዳንዶች የፍቅር ጓደኛ መያዝ እንዲሁ ለመዝናናት ብቻ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ግን “የፍቅር ጓደኝነት” የሚለው አገላለጽ የተሠራበት፣ አንድ ወንድና አንዲት ሴት በትዳር መጣመር ይችሉ እንደሆነ ለማወቅ አብረው የሚያሳልፉትን ጊዜ ለማመልከት ነው። ስለዚህ አንድ ሰው የፍቅር ጓደኝነት የሚመሠርተው በዓላማ ነው። ከተቃራኒ ፆታ ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ሲል ብቻ የሚያደርገው ነገር አይደለም።

 የፍቅር ጓደኝነት የጀመሩ ሰዎች ውሎ አድሮ ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፦ ወይ ለመጋባት አሊያም ግንኙነቱን ለማቆም። የፍቅር ጓደኝነት ስትጀምር ከሁለቱ አንዱ እንደሚሆን ጠብቀህ መግባት አለብህ።

 ዋናው ነጥብ፦ የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመር እንደደረስክ ከተሰማህ፣ ትዳር ለመመሥረት ዝግጁ እንደሆንክ እርግጠኛ ነህ ማለት ነው።

ለማግባት ሳታስብ የፍቅር ጓደኝነት መጀመር፣ ሥራ የመያዝ ዓላማ ሳይኖርህ የቅጥር ቃለ መጠይቅ እንደማድረግ ነው

የፍቅር ጓደኛ ለመያዝ ደርሰሃል?

  የፍቅር ጓደኝነት ወደ ትዳር ሊያመራ ይችላል፤ በመሆኑም ያሉህን ባሕርያት በመገምገም ምን ዓይነት የትዳር ጓደኛ ልትሆን እንደምትችል ቆም ብለህ ማሰብህ ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ከዚህ በታች የቀረቡትን ነጥቦች ልታስብባቸው ትችላለህ፦

  •   ከቤተሰብህ ጋር ያለህ ግንኙነት። ወላጆችህን ወይም ወንድሞችህንና እህቶችህን የምትይዝበት መንገድ በተለይ ደግሞ ውጥረት ውስጥ ስትሆን፣ ብታገባ የትዳር ጓደኛህን እንዴት እንደምትይዛት ይጠቁማል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ እንዲሁም ክፋት ሁሉ ከእናንተ መካከል ይወገድ።”—ኤፌሶን 4:31

     ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ወላጆቼ ወይም ወንድሞቼና እህቶቼ ቢጠየቁ በአክብሮት እንደምይዛቸው ይናገራሉ? ከእነሱ ጋር አለመግባባት ሲያጋጥመኝ በተረጋጋ መንፈስ አነጋግራቸዋለሁ? ወይስ ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ ነገሩ ወደ ጭቅጭቅ ያመራል?’

    ከወላጆችህ ጋር አለመግባባት ሲፈጠር በአግባቡ መፍታት የማትችል ከሆነ ከትዳር ጓደኛህ ጋር ይህን ማድረግ የምትችል ይመስልሃል?

  •   የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ። ትዳር ስትመሠርት የትዳር ጓደኛህን ፍላጎት ግምት ውስጥ ማስገባትና አብዛኛውን ጊዜ ለእሷ ምርጫ ቅድሚያ መስጠት ይኖርብሃል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ።”—1 ቆሮንቶስ 10:24

     ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘እኔ ያልኩት ካልሆነ ብዬ ችክ እላለሁ? ሌሎች ምክንያታዊ እንደሆንኩ ይሰማቸዋል? ከራሴ ፍላጎት ይልቅ ሌሎች ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ቅድሚያ እንደምሰጥ እያሳየሁ ያለሁት እንዴት ነው?’

  •   ትሕትና። ጥሩ የትዳር ጓደኛ ስህተቱን አምኖ ይቀበላል እንዲሁም ከልብ ይቅርታ ይጠይቃል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሳሳታለን።”—ያዕቆብ 3:2 የግርጌ ማስታወሻ

     ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ስህተቴን ወዲያው አምኜ እቀበላለሁ ወይስ ሰበባ ሰበብ እደረድራለሁ? ሌሎች ማሻሻል ያለብኝን ነገር ሲነግሩኝ ቶሎ ይከፋኛል?’

  •   ገንዘብ አያያዝ። አብዛኞቹ ባለትዳሮች ከሚጨቃጨቁባቸው ነገሮች አንዱ ገንዘብ አያያዝ ነው፤ በዚህ ረገድ ጠንቃቃ ከሆንክ እንዲህ ያለውን ውዝግብ ማስቀረት ትችላለህ።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?”—ሉቃስ 14:28

     ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ገንዘቤን የምጠቀምበት በአግባቡ ነው ወይስ ሁልጊዜ ዕዳ ውስጥ እገባለሁ? በገንዘብ አያያዝ ረገድ ኃላፊነት የሚሰማኝ እንደሆንኩ እያሳየሁ ነው?’

  •   መንፈሳዊነት። የይሖዋ ምሥክር ከሆንክ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ሊኖርህ ይገባል፤ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ላይ አዘውትረህ የምትገኝ መሆን አለብህ።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው።”—ማቴዎስ 5:3

     ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘መንፈሳዊነቴን ለመጠበቅ በራሴ ጥረት አደርጋለሁ? ለመንፈሳዊነቴ ቅድሚያ እሰጣለሁ ወይስ ሌሎች ነገሮች ትኩረቴን እንዲሰርቁት እፈቅዳለሁ?’

 ዋናው ነጥብ፦ ለምታገባት ሴት ጥሩ የትዳር ጓደኛ ልትሆንላት ይገባል። እንዲህ ዓይነት ሰው ለመሆን ጥረት እያደረግህ ከሆነ አንተም ጥሩ የትዳር ጓደኛ ልታገኝ ትችላለህ።