የወጣቶች ጥያቄ
ጥሩ አርዓያ የሚሆነኝን ሰው መምረጥ የምችለው እንዴት ነው?
“በትምህርት ቤት ውስጥ ችግር በሚያጋጥመኝ ወቅት ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞት የነበረን አንድ የማደንቀው ሰው ለማሰብ እሞክራለሁ። ከዚያም የዚያን ሰው ምሳሌ ለመከተል ጥረት አደርጋለሁ። አርዓያ የሚሆነኝ ሰው ማግኘቴ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን በቀላሉ እንድወጣ ረድቶኛል።”—ሄሊ
አርዓያ የሚሆንህ ሰው ማግኘትህ ችግር ውስጥ እንዳትገባ እንዲሁም ግቦችህ ላይ እንድትደርስ ይረዳሃል። ዋናው ነገር ጥሩ አርዓያ የሚሆንህን ሰው መምረጥህ ነው።
አርዓያ የሚሆንህን ሰው በጥንቃቄ መምረጥህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
አርዓያ አድርገህ የምትመርጠው ሰው ማንነት በምታሳየው ምግባር ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖች ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ትኩረት ሰጥተው እንዲመለከቱ ያበረታታል፤ “ምግባራቸው ያስገኘውን ውጤት በሚገባ በማጤን በእምነታቸው ምሰሏቸው” ይላል።—ዕብራውያን 13:7
ጠቃሚ ምክር፦ አርዓያ አድርገህ የምትመርጣቸው ሰዎች ጥሩም ሆነ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ ይችላሉ። በመሆኑም አርዓያ አድርገህ ልትመርጥ የሚገባው ጥሩ ባሕርይ ያላቸውን ሰዎች ብቻ ነው፤ አንድ ሰው በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ስለሆነ ወይም እኩያህ ስለሆነ ብቻ አርዓያህ አድርገህ ልትመርጠው አይገባም።
“አዳም ከተባለ አንድ ክርስቲያን ብዙ ነገር ተምሬያለሁ፤ ለነገሮች ያለው አመለካከትና ባሕርይው ብዙ ነገር አስተምሮኛል። የሚገርመው፣ እሱ የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ጥቃቅን ነገሮች ሳይቀር አሁንም ድረስ አስታውሳለሁ። በሕይወቴ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳሳደረ እሱም እንኳ የሚያውቅ አይመስለኝም።”—ኮለን
አርዓያ አድርገህ የምትመርጠው ሰው ማንነት በአስተሳሰብህና በስሜትህ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።”—1 ቆሮንቶስ 15:33
ጠቃሚ ምክር፦ አንድ ሰው ውጫዊ ገጽታው ስለማረከህ ብቻ አርዓያህ አድርገህ ልትመርጠው አይገባም፤ አርዓያ አድርገህ የምትመርጠው ሰው ማራኪ ባሕርያት ሊኖሩት ይገባል። አለዚያ ውሎ አድሮ ለሐዘን ልትዳረግ ትችላለህ።
“ቆንጆ ከሆኑ ሰዎች ጋር ሁልጊዜ ራሳችንን የምናወዳድር ከሆነ ምንም እንደማንረባና በጣም አስቀያሚ እንደሆንን ሊሰማን ይችላል። ይህ ደግሞ ከልክ በላይ ለመልካችን እንድንጨነቅ ሊያደርገን ይችላል።”—ታማራ
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ታዋቂ ሰዎችንና ስፖርተኞችን እንደ አርዓያ አድርጎ መመልከት ምን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል?
አርዓያ አድርገህ የምትመርጠው ሰው ማንነት ግብህ ላይ እንድትደርስ ወይም እንዳትደርስ ሊያደርግህ ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል፤ ከሞኞች ጋር የሚገጥም ግን ጉዳት ይደርስበታል።”—ምሳሌ 13:20
ጠቃሚ ምክር፦ ልታዳብራቸው የምትፈልጋቸውን ጥሩ ባሕርያት የሚያንጸባርቁ ሰዎችን አርዓያ አድርገህ ምረጥ። እነዚህን ሰዎች በትኩረት መመልከትህ ግብህ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ እንዳለብህ ሊጠቁምህ ይችላል።
“‘ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን እፈልጋለሁ’ እንደሚለው ዓይነት ግልጽ ያልሆነ ግብ ከማውጣት ይልቅ ‘ልክ እንደ ጄን ኃላፊነት የሚሰማኝ ሰው መሆን እፈልጋለሁ። እሷ ሁልጊዜ ሰዓት ታከብራለች፤ እንዲሁም የተሰጣትን ሥራ በቁም ነገር ታከናውናለች’ ብትል ይበልጥ ውጤታማ ልትሆን ትችላለህ።”—ሚርያም
ዋናው ነጥብ፦ ጥሩ አርዓያ ሊሆንህ የሚችል ሰው መምረጥህ የምትፈልገውን ዓይነት ሰው ለመሆን ይረዳሃል።
ጥሩ አርዓያ የሚሆንህን ሰው መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው?
አርዓያ የሚሆንህን ሰው ለመምረጥ ከታች ከተገለጹት ሁለት መንገዶች አንዱን ልትጠቀም ትችላለህ።
ልታዳብረው የምትፈልገውን ባሕርይ ምረጥ፤ ከዚያም ያን ባሕርይ የሚያንጸባርቅ ሰው ለማግኘት ሞክር።
የምታደንቀውን አንድ ሰው ምረጥ፤ ከዚያም ግለሰቡ ካሉት ባሕርያት መካከል የትኛውን ማዳበር እንደምትፈልግ አስብ።
ከዚህ ርዕስ ጋር አብሮ ያለው የመልመጃ ሣጥን ይህን እንድታደርግ ሊረዳህ ይችላል።
አርዓያ አድርገህ ከምትመለከታቸው ሰዎች መካከል የሚከተሉት ሰዎች ሊካተቱ ይችላሉ፦
እኩዮችህ። “እንደ አርዓያ አድርጌ የምመለከታት በጣም የምቀርባት ጓደኛዬን ነው። ምንም ያህል ሥራ ቢበዛበት ለሌሎች ሰዎች አሳቢነት ከማሳየት ወደኋላ አትልም። በዕድሜ ከእኔ የምታንስ ብትሆንም እኔ የሌሉኝ ግሩም ባሕርያት አሏት፤ ይህም የእሷን አርዓያ ለመከተል ያነሳሳኛል።”—ሚርያም
ትላልቅ ሰዎች። ወላጆችህን ወይም የእምነት ባልንጀሮችህ የሆኑ ሌሎች ትላልቅ ሰዎችን አርዓያ አድርገህ ልትመርጥ ትችላለህ። “ሁለቱም ወላጆቼ ለእኔ አርዓያ ናቸው። ግሩም ባሕርያት አሏቸው። ጉድለት እንዳለባቸው አውቃለሁ፤ ሆኖም ጉድለት እያለባቸውም ታማኝ ሆነው ቀጥለዋል። እኔም የእነሱ ዕድሜ ላይ ስደርስ እንዲህ እንዲባልልኝ እፈልጋለሁ።”—አኔት
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች። “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ሰዎች መካከል አርዓያ የሚሆኑኝ ብዙ ሰዎች መርጫለሁ፤ ከእነሱም መካከል ጢሞቴዎስ፣ ሩት፣ ኢዮብ፣ ጴጥሮስና ትንሿ እስራኤላዊት ልጃገረድ ይገኙበታል፤ ሁሉንም አርዓያ አድርጌ የመረጥኳቸው በተለያየ ምክንያት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት ሰዎች ይበልጥ ባወቅኩ መጠን ሰዎቹ ይበልጥ እውን እየሆኑልኝ ይሄዳሉ። በእምነታቸው ምሰሏቸው የተባለውን መጽሐፍ እንዲሁም ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች በተባለው መጽሐፍ ሁለቱም ጥራዞች ላይ ‘አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች ማውጫ’ በሚለው ሥር የወጡትን ርዕሶች ማንበብ በጣም ያስደስተኛል።”—ሜሊንዳ
ጠቃሚ ምክር፦ አርዓያ የሚሆን አንድ ሰው ብቻ በመምረጥ አትወሰን። ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷቸዋል፦ “እኛ ከተውንላችሁ ምሳሌ ጋር በሚስማማ መንገድ የሚመላለሱትን ሁሉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ።”—ፊልጵስዩስ 3:17
ይህን ታውቅ ነበር? አንተም ለሌላ ሰው አርዓያ መሆን ትችላለህ! መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ታማኞች ለሆኑት በንግግር፣ በምግባር፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና አርዓያ ሁን።”—1 ጢሞቴዎስ 4:12
“አንተ ራስህ የምታሻሽለው ነገር ቢኖርህም ሌሎች የተሻሉ ሰዎች እንዲሆኑ ልትረዳ ትችላለህ። የምታደርገውን ነገር ማን እየተመለከተ እንዳለ እንዲሁም የምትናገረው ነገር የአንድን ሰው ሕይወት ሊለውጥ የሚችለው እንዴት እንደሆነ አታውቅም።”—ኪያና