የይሖዋ ምሥክሮች ለትምህርት ምን አመለካከት አላቸው?
ለትምህርት ያለን አመለካከት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት መመሪያዎች ላይ የተመሠረተ ነው። ሆኖም እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር እነዚህን መመሪያዎች ተግባራዊ ከሚያደርግበት መንገድ ጋር በተያያዘ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናውን መጠቀም ይኖርበታል። ከእነዚህ መመሪያዎች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት። a
ትምህርት በጣም አስፈላጊ ነው
ትምህርት ‘ጥበብና የማመዛዘን ችሎታ’ ለማዳበር ይረዳል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ለእነዚህ ባሕርያት ትልቅ ቦታ ይሰጣል። (ምሳሌ 2:10, 11፤ 3:21, 22) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ተከታዮቹ እሱ ያዘዛቸውን ነገር ለሌሎች ማስተማር እንዳለባቸው ተናግሯል። (ማቴዎስ 28:19, 20) በመሆኑም በጉባኤዎቻችን ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁለገብ እውቀት እንዲኖራቸው ማለትም የማንበብ፣ የመጻፍና ከሌሎች ጋር የመወያየት ችሎታ እንዲያዳብሩ b እንዲሁም ስለ ሌሎች ሃይማኖቶችና ባሕሎች እንዲያውቁ እናበረታታለን ብሎም እንረዳለን።—1 ቆሮንቶስ 9:20-22፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:13
መንግሥታትም ቢሆኑ ትምህርት አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ፤ በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዲማሩ ያዝዛሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ” ስለሚል መንግሥታት የሚያወጧቸውን እንዲህ ያሉ ሕጎች እናከብራለን። (ሮም 13:1) በተጨማሪም ልጆቻችን እንዲሁ ከክፍል ክፍል እንዲያልፉ ብቻ ሳይሆን ተግተው እንዲማሩና ጥሩ ውጤት ለማምጣት የቻሉትን ያህል ጥረት እንዲያደርጉ እናበረታታለን። c የአምላክ ቃል “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት” ይላል።—ቆላስይስ 3:23 አዲሱ መደበኛ ትርጉም
ትምህርት ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማቅረብ ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው የራሱ ለሆኑት በተለይ ደግሞ ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን የካደ ከመሆኑም በላይ እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ትምህርት አምላክ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን እንድናቀርብ የሰጠንን ኃላፊነት ለመወጣት ይረዳናል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚገልጸው የትምህርት ዋነኛ ዓላማ “ሰዎች በኢኮኖሚው ዘርፍ አስተዋጽኦ በማበርከት . . . ፍሬያማ የማኅበረሰቡ አባል እንዲሆኑ መርዳት ነው።” ጥሩ ችሎታ ያለውና በሚገባ የተማረ ሰው፣ ችሎታ ከሌለውና መሠረታዊ ትምህርት ካልተማረ ሰው በተሻለ መልኩ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ማቅረብ ይችላል።—ምሳሌ 22:29
በተጨማሪም ወላጆች ልጆቻቸውን አዋቂ ሆነው ለሚመሩት ሕይወት ሊያዘጋጇቸው ይገባል፤ መደበኛ ትምህርት ደግሞ በዚህ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። (2 ቆሮንቶስ 12:14) እርግጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ትምህርት በነፃ አይሰጥ ይሆናል፤ አሊያም መደበኛ ትምህርት ማግኘት ከባድ ሊሆን ወይም ልጆችን ማስተማር ከአካባቢው ባሕል ጋር ሊጋጭ ይችላል። ያም ቢሆን ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ እናበረታታለን። d ከዚህም ባለፈ ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ ተማሪዎች እንዲሆኑ መርዳት የሚችሉበትን መንገድ በተመለከተ ጠቃሚ ምክር እንሰጣለን። e
ለትምህርት ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል
ያሉትን የትምህርት አማራጮች በጥንቃቄ እንመረምራለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል” ይላል። (ምሳሌ 14:15) በዚህ ምክር መሠረት፣ ተጨማሪ ትምህርት (ሁለተኛ ደረጃን ካጠናቀቅን በኋላ የሚሰጥ ትምህርት) ለመከታተል የሚያስችሉ አማራጮችን በጥንቃቄ እንመረምራለን፤ እንዲሁም እያንዳንዱ አማራጭ የሚጠይቀውን ወጪና የሚያስገኘውን ጥቅም እናጤናለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ዓይነት ሙያ ብንማር በአንጻራዊ ሁኔታ አጠር ባለ ጊዜ ውስጥ ጥሩ ሥልጠና ማግኘት እንችላለን።
መንፈሳዊ ትምህርት ከዓለማዊ ትምህርት የላቀ ዋጋ አለው። ከዓለማዊ ትምህርት በተለየ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መንፈሳዊ ትምህርት ስለ አምላክ ለማወቅ ያስችላል፤ ይህ እውቀት ደግሞ መዳን ያስገኝልናል። (ዮሐንስ 17:3) በተጨማሪም መንፈሳዊ ትምህርት የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ያስተምረናል፤ በመሆኑም “ጽድቅ፣ ፍትሕና ትክክል የሆነውን ነገር ይኸውም የጥሩነትን ጎዳና በሙሉ” እንረዳለን። (ምሳሌ 2:9) ሐዋርያው ጳውሎስ በዛሬው ጊዜ ካለው የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ጋር የሚመጣጠን ሥልጠና ወስዶ ነበር፤ ሆኖም ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ የሚገልጸው እውቀት “የላቀ ዋጋ [እንዳለው]” ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 3:8፤ የሐዋርያት ሥራ 22:3) በተመሳሳይም በዘመናችን የሚኖሩ ከፍተኛ ትምህርት የተከታተሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች፣ መንፈሳዊ ትምህርት የላቀ ዋጋ እንዳለው ያምናሉ። f
ከፍተኛ ትምህርት ለሥነ ምግባራዊና ለመንፈሳዊ አደጋ ያጋልጣል
መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) የይሖዋ ምሥክሮች፣ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎችና ከፍተኛ ትምህርት በሚሰጥባቸው ሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት ውስጥ ያለው ሁኔታ ለሥነ ምግባራዊና ለመንፈሳዊ አደጋ እንደሚያጋልጥ ይሰማቸዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ገብተው ላለመማር መርጠዋል፤ ወላጆችም ቢሆኑ ልጆቻቸውን ላለመላክ ወስነዋል። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተሳሳቱ ሐሳቦች ለማስፋፋት እንደሚሞክሩ አስተውለዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦
የተሳሳተ አመለካከት፦ ገንዘብ ደስታ ለማግኘትና አስተማማኝ ሕይወት ለመምራት ያስችላል
ብዙ ሰዎች ከፍተኛ ትምህርት መከታተል ዳጎስ ያለ ደሞዝ ለማግኘት አስተማማኝ የሆነው መንገድ እንደሆነ ይናገራሉ፤ በዚህም የተነሳ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ በርካታ ተማሪዎች ብዙ ገንዘብ ማግኘት ስለሚፈልጉ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ይማራሉ። አንዳንዶች ገንዘብ ደስታ ለማግኘትና አስተማማኝ ሕይወት ለመምራት እንደሚያስችላቸው ተስፋ ያደርጋሉ፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ከንቱ እንደሆነ በግልጽ ይናገራል። (መክብብ 5:10) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር” እንደሆነና ከእምነት ጎዳና ሊያስወጣ እንደሚችል ያስተምራል። (1 ጢሞቴዎስ 6:10) የይሖዋ ምሥክሮች “ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” ወጥመድ እንዳይሆንባቸው ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።—ማቴዎስ 13:22
የተሳሳተ አመለካከት፦ ከፍተኛ ትምህርት ክብር ወይም ከፍ ያለ ቦታ ያስገኛል
የቀድሞው የጆርጂያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ኒካ ጊሎሪ በአገራቸው ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ስላላቸው አመለካከት የሚከተለውን ሐሳብ ጽፈዋል፦ “ጆርጂያ ውስጥ በሌሎች ዘንድ ከፍ ያለ ግምት ለማግኘት የዩኒቨርስቲ ዲግሪ የግድ አስፈላጊ ነው ሊባል ይችላል። . . . [ቀደም ባሉት ጊዜያት] ዲግሪ የሌላቸው ወጣቶች ቤተሰቦቻቸውን እንዳዋረዱ ይቆጠሩ ነበር።” g ከዚህ በተቃራኒ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ዓለም ውስጥ ትልቅ ቦታ ላይ ለመድረስ መጣጣር ስላለው አደጋ ያስጠነቅቃል። ኢየሱስ በሌሎች ዘንድ ክብር ለማግኘት የሚመኙትን በዘመኑ የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች “እርስ በርሳችሁ ክብር የምትሰጣጡ . . . ሆናችሁ ሳላችሁ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 5:44) በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለው አጠቃላይ መንፈስ ሰዎች አምላክ የሚጠላውን የትዕቢት ዝንባሌ እንዲያዳብሩ ያደርጋል።—ምሳሌ 6:16, 17፤ 1 ጴጥሮስ 5:5
የተሳሳተ አመለካከት፦ እያንዳንዱ ሰው ትክክልና ስህተት የሆኑትን ነገሮች በተመለከተ የራሱን መሥፈርት ሊያወጣ ይገባል
የይሖዋ ምሥክሮች ትክክልና ስህተት የሆኑትን ነገሮች በተመለከተ አምላክ ያወጣውን መሥፈርት ይከተላሉ። (ኢሳይያስ 5:20) ጆርናል ኦቭ አልኮሆል ኤንድ ድራግ ኤጁኬሽን በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ ርዕስ እንደገለጸው ግን በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያለው የእኩዮች ተጽዕኖ፣ በርካታ ተማሪዎች “ትክክልና ስህተት ስለሆኑ ነገሮች ቀደም ሲል ከነበራቸው እውቀት ጋር የሚቃረን ውሳኔ እንዲያደርጉ ይገፋፋቸዋል።” h ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሚገኘው “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” ከሚለው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አልኮል ከልክ በላይ እንደ መጠጣት፣ አደገኛ ዕፆችን እንደ መውሰድ እንዲሁም ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት እንደ መፈጸም ያሉ አምላክ የሚያወግዛቸው ድርጊቶች የተለመዱ አልፎ ተርፎም የሚበረታቱ ነገሮች ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1
የተሳሳተ አመለካከት፦ ዓለምን ለማሻሻል ከሁሉ የተሻለው መንገድ ከፍተኛ ትምህርት መከታተል ነው
ብዙዎች ከፍተኛ ትምህርት የሚከታተሉት ሀብት ወይም ዝና ለማግኘት አሊያም ተገቢ ያልሆነ ነገር በመፈጸም የሚገኘውን ደስታ ለማጣጣም እንዳልሆነ እንገነዘባለን፤ ከዚህ ይልቅ ራሳቸውንም ሆነ ዓለምን ለማሻሻል ስለሚፈልጉ ነው። ይህ ጥሩ ግብ እንደሆነ አይካድም፤ ሆኖም እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ለማድረግ የሚያስችል ሌላ መንገድ መርጠናል። ልክ እንደ ኢየሱስ፣ የተሻለ ዓለም የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ እናምናለን። (ማቴዎስ 6:9, 10) ይህ ሲባል ግን የአምላክ መንግሥት በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች እስኪያስወግድ ድረስ እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጣለን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመላው ምድር እንሰብካለን፤ ይህ ምሥራች በየዓመቱ፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ እየረዳ ነው። i—ማቴዎስ 24:14
a ከወላጆቻቸው ጋር የሚኖሩ ወጣቶች፣ ትምህርትን በተመለከተ ወላጆቻቸው የሚሰጧቸውን መመሪያ መከተል ይኖርባቸዋል፤ ሆኖም እንዲህ ማድረግ ያለባቸው የወላጆቻቸው መመሪያ ከአምላክ ሕጎች ጋር እስካልተጋጨ ድረስ ብቻ ነው።—ቆላስይስ 3:20
b ለዚህም ስንል፣ ማንበብና መጻፍ ለመማር የሚረዱ ጽሑፎችን ከ11 ሚሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎች አዘጋጅተናል፤ ከእነዚህ መካከል ማንበብና መጻፍ መማር (እንግሊዝኛ) የተባለው ብሮሹር ይገኝበታል። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ በ120 ቋንቋዎች መሠረተ ትምህርት እናስተምራለን። ከ2003 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት ውስጥ ወደ 70,000 የሚጠጉ ሰዎችን ማንበብና መጻፍ አስተምረናል።
c “ትምህርቴን ባቋርጥ ይሻል ይሆን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
d ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆች ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ እናበረታታለን። በመጋቢት 15, 2003 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ልጄን ትምህርት ቤት ማስገባት ይኖርብኛል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
e “ልጃችሁ የትምህርት ውጤቱን እንዲያሻሽል መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
f “ስለ ሕይወት አመጣጥ የተሰጡ አስተያየቶች” የሚለውን jw.org ላይ የሚገኝ ክፍል ተመልከት።
g ፕራክቲካል ኢኮኖሚክስ፦ ኢኮኖሚክ ትራንስፎርሜሽን ኤንድ ገቨርንመንት ሪፎርም ኢን ጆርጂያ 2004—2012 ገጽ 170
h ጥራዝ 61፣ ቁ. 1፣ ሚያዝያ 2017 ገጽ 72
i የአምላክ ቃልና ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው መልእክት ያላቸውን ኃይል የሚያሳዩ እውነተኛ ታሪኮችን ለማንበብ jw.org ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” የሚለውን ክፍል ተመልከት።