በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

“ይሖዋ ሕይወታችንን አትርፎልናል”

“ይሖዋ ሕይወታችንን አትርፎልናል”

 ሳውባጊያ የምትባል በሕንድ የምትኖር አንዲት ሴት በ2005 የምትወደውን ባሏን በሞት አጣች። ባለቤቷ እሷንና ሜጋና የተባለችውን የሦስት ዓመት ልጃቸውን በሚገባ ይንከባከባቸው ነበር። አሁን ግን ሳውባጊያ የሚያስፈልጋቸውን ማሟላት ተፈታታኝ ሆነባት።

 ይህም እንዳይበቃ ደግሞ ሰዎች ሳውባጊያን ያገልሏት ጀመር። ቤተሰቧ፣ እሷንና ልጇን እንደ ለማኝ ቆጠሯቸው፤ ሸክም እንደሆነችባቸው ደጋግመው ይነግሯት ነበር። ሳውባጊያ መጽናኛ ባገኝ ብላ በአካባቢዋ ወደሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ሄደች። ሆኖም እዚያ ያሉት ሰዎች ድሃ በመሆኗ ናቋት። ሳውባጊያ በኢኮኖሚ ራሷን ለመቻል ሥራ መፈለግ ጀመረች። የሚያሳዝነው ግን ሥራ ለማግኘት ብዙ ጥረት ብታደርግም አልተሳካላትም።

 ሳውባጊያ እንዲህ ብላለች፦ “ተስፋ ስለቆረጥኩ ሕይወቴን ለማጥፋት ወሰንኩ። እኔ ከሌለሁ ግን ልጄ ብዙ ችግሮች እንደሚያጋጥሟት አውቃለሁ። ስለዚህ የሁለታችንንም ሕይወት ለማጥፋት ወሰንኩ።” ዋጋ እንደሌላትና ማንም እንደማይወዳት ስለተሰማት መርዝ ለመግዛት ሄደች።

 ሳውባጊያ በባቡር ወደ ቤቷ እየተመለሰች ሳለ ኤሊዛቤት የተባለች አንዲት የይሖዋ ምሥክር አነጋገረቻት። ሳውባጊያ ሥራ እንደሌላት ስትነግራት ኤሊዛቤት ሥራ ለማግኘት ልትረዳት እንደምትችል ገለጸችላት። ኤሊዛቤት ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት እየሄደች እንደሆነም ነገረቻት። ይህ ሳውባጊያን አስገረማት፤ ከዚያ በፊት ወደ ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች የሄደች ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ስለ ማጥናት ሰምታ አታውቅም። ኤሊዛቤት መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠናው እንዴት እንደሆነ ለማየት ቤቷ እንድትመጣ ሳውባጊያን ጋበዘቻት።

 ሳውባጊያ ቤቷ ስትደርስ ሕይወቷን ለማጥፋት የነበራት ዕቅድ አልተቀየረም ነበር። ሆኖም አንዲት ዘመዳቸው ሜጋናን ይዛት ስለተጓዘች ሳውባጊያ ያሰበችውን ለመፈጸም ልጇ እስክትመለስ ለመጠበቅ ወሰነች።

 በዚህ መሃል ኤሊዛቤትን ለመጠየቅ ሄደች፤ ኤሊዛቤትም ደስ ብሏት ተቀበለቻት። በውይይታቸው መሃል ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ አሳየቻት። “ሙታን የት ናቸው?” የሚለው ምዕራፍ የሳውባጊያን ትኩረት ሳበው። ምዕራፉ ቀልቧን የሳበው ባለቤቷ የሞተባት በቅርቡ ስለሆነ ነው። ሳውባጊያ በዚያኑ ዕለት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማች።

 ኤሊዛቤት፣ ሳውባጊያን በቀጣዩ ሳምንት በሚደረግ የክልል ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ጋበዘቻት፤ እሷም በክልል ስብሰባው ላይ ለመገኘት ተስማማች። ስብሰባውን በጣም ስለወደደችው የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ወሰነች። ከክልል ስብሰባው ስትመለስ ደግሞ ሥራ አገኘች።

 ሳውባጊያ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቷን ቀጠለች። አሁን ሕይወቷ ዓላማ እንዳለው ስለሚሰማት ራሷን ማጥፋት አትፈልግም። መጀመሪያ ሳውባጊያ፣ ቆየት ብሎም ልጇ ሜጋና ተጠመቁ። አሁን ሁለቱም የዘወትር አቅኚዎች ናቸው፤ ሜጋናም በሕንድ ከሚገኙ የትርጉም ቢሮዎች በአንዱ የርቀት ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆና ታገለግላለች።

ሳውባጊያ እና ሜጋና በአሁኑ ወቅት

 ሳውባጊያ እና ሜጋና፣ ኤሊዛቤት ሳውባጊያን ባቡር ላይ ቀርባ ስላነጋገረቻት፣ ልባዊ አሳቢነት ስላሳየቻትና ስለ እውነት ስለነገረቻት በጣም ያመሰግኗታል! ይሖዋ ላደረገላቸው ነገርም ጥልቅ የአመስጋኝነት ስሜት አላቸው። ሜጋና እንዲህ ብላለች፦ “ያን ዕለት እውነትን ባንሰማ ኖሮ ይሄኔ ሞተን ተረስተን ነበር። አሁን በሕይወታችን ደስተኞች ነን። እኔና እናቴ፣ አባቴን እንደገና እቅፍ የምናደርግበትን ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን፤ ያን ጊዜ ስለ ይሖዋ እናስተምረዋለን፣ ሕይወታችንን እንዴት እንዳተረፈልንም እንነግረዋለን።”