የማሮኒ ወንዝን ተከትሎ የተካሄደ ዘመቻ
በደቡብ አሜሪካ በአማዞን ደን ውስጥ ከከተማ ርቀው የሚኖሩ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ጎሳዎች አሉ። በመሆኑም ሐምሌ 2017 13 የይሖዋ ምሥክሮች የማሮኒ ወንዝንና በፍሬንች ጊያና የሚገኙትን ገባሮቹን ተከትለው አንድ ዘመቻ አካሂደው ነበር። የዘመቻው ዓላማ ተስፋ ሰጪ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በወንዙ ዳርቻ ለሚኖሩት ሰዎች ማዳረስ ነበር።
ለዘመቻው መዘጋጀት
የ12 ቀን ዘመቻው ከመጀመሩ አንድ ወር አስቀድሞ በተደረገው የዝግጅት ስብሰባ ላይ ሁሉም ተሳታፊዎች ተገኝተው ነበር። ዊንስሊ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ አካባቢውና ስለ ታሪኩ አጠናን፤ እንዲሁም ለጉዞው ራሳችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተወያየን።” ሁሉም ተሳታፊዎች ሃሞክ (በሁለት ነገሮች ላይ ታስሮ የሚንጠለጠል መተኛ ጨርቅ) እና አጎበር የሚከቱበት ውኃ የማያስገባ መያዣ ተሰጣቸው። ጉዞው ሁለት ጊዜ በአውሮፕላን መሳፈርን እንዲሁም ለበርካታ ሰዓታት በጀልባ መጓዝን የሚጠይቅ ነበር።
በዘመቻው እንዲካፈሉ የተመረጡት ሰዎች ስለ ዘመቻው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰሙ ምን ተሰማቸው? በ60ዎቹ ዕድሜ የሚገኙት ክሎድና ሊዜት ግብዣውን ወዲያውኑ ተቀበሉ። ክሎድ “በጣም ደስ ብሎኝ የነበረ ቢሆንም ትንሽ ፈርቼ ነበር። ወንዙ አንዳንድ ቦታዎች ላይ አደገኛ እንደሆነ ሰምቼ ነበር” ብሏል። ሊዜት ደግሞ “የአካባቢውን ቋንቋ መናገር አለመቻሌ አሳስቦኝ ነበር” ብላለች።
ሚካኤል የተባለ ተሳታፊም ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ዋያና ጎሳ ብዙም የምናውቀው ነገር አልነበረም። ስለዚህ አንዳንድ ቃላትን ለመማርና የቋንቋውን ሰላምታ ለማወቅ ኢንተርኔት ላይ ምርምር አደረግኩ።”
ከባለቤቷ ከዮሃን ጋር የተጓዘችው ሸርሊ በወንዙ ዳርቻ ባሉት መንደሮች ውስጥ የሚነገሩትን ቋንቋዎች ዝርዝር ጽፋ ነበር። “በአብዛኛዎቹ ቋንቋዎች ቪዲዮዎችን ከjw.org ላይ አወረድን፤ እንዲሁም በዋያና ቋንቋ የተወሰነ ለመግባባት የሚረዳ መጽሐፍ ገዛን” ብላለች።
የተለያዩ ጎሳዎችን ለማግኘት ያደረጉት ጉዞ
የቡድኑ አባላት ማክሰኞ፣ ሐምሌ 4 ከሳን ለሬን ዱ ማሮኒ አውሮፕላን ተሳፍረው በፍሬንች ጊያና ወደምትገኘው ማሪፓሱላ የተባለች ትንሽ ከተማ ሄዱ።
የቡድኑ አባላት ለቀጣዮቹ አራት ቀናት ፒሮግ ተብሎ በሚጠራ ባለሞተር ጀልባ እየተጓዙ በማሮኒ ወንዝ ዳርቻ ባሉ መንደሮች ለሚኖሩ ሰዎች ሰበኩ። ከቡድኑ አባላት አንዱ የሆነው ሮላን እንዲህ ብሏል፦ “የአካባቢው ነዋሪዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው። ብዙ ጥያቄዎች አሏቸው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስን እንድናስጠናቸው ፈልገው ነበር።”
ዮሃንና ሸርሊ በአንዱ መንደር ውስጥ አንድ ወጣት ባልና ሚስት አነጋግረው ነበር፤ እነዚህ ባልና ሚስት በቅርቡ አንዷ ዘመዳቸው ራሷን አጥፍታ ነበር። ዮሃን እንዲህ ብሏል፦ “[በJW ብሮድካስቲንግ ላይ የወጣውን] አንድ የአሜሪካ ጎሳ ተወላጅ ፈጣሪውን አወቀ የተባለውን ቪዲዮ አሳየናቸው። ባልና ሚስቱ በቪዲዮው ልባቸው በእጅጉ ተነካ። ከእኛ ጋር መወያየታቸውን መቀጠል ስለፈለጉ የኢ-ሜይል አድራሻቸውን ሰጡን።”
በወንዙ የላይኛው ተፋሰስ የጎበኙት የመጨረሻው ሩቅ መንደር አንቴኩም ፓታ የተባለው መንደር ነበር። በዚያም የመንደሩ መሪ በጉዞ የደከሙት የይሖዋ ምሥክሮች ሃሞካቸውን በመንደሩ ውስጥ እንዲያንጠለጥሉ ፈቀደላቸው። ከዚያም እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ወንዝ ወርደው ገላቸውን ታጠቡ።
የቡድኑ አባላት ከዚያ ተነስተው ትዌንኬ ወደተባለ መንደር ሄዱ። በዚያም የመንደሩ ነዋሪዎች ለቅሶ ላይ ሆነው አገኟቸው። ዘመቻውን ካደራጁት ወንድሞች አንዱ የሆነው ኤሪክ እንዲህ ብሏል፦ “የጎሳው መሪ በመንደሩ ውስጥ እየተዘዋወርን ሐዘንተኞቹን እንድናጽናና ፈቀደልን። የጎሳው መሪና ቤተሰቦቹ በዋያና ቋንቋ ከተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ባነበብንላቸው ጥቅሶች በጣም ተደሰቱ። በተጨማሪም ስለ ትንሣኤ ተስፋ የሚናገሩ ቪዲዮዎችን አሳየናቸው።”
ወደ ግራን ሶንቲ እና አፓቱ መጓዝ
ከዚህ በመቀጠል የቡድኑ አባላት ከማሪፓሱላ ተነስተው ለግማሽ ሰዓት በአውሮፕላን በመጓዝ ግራን ሶንቲ ወደተባለች ትንሽ ከተማ ደረሱ። ማክሰኞ እና ረቡዕ የዘመቻው ተሳታፊዎች ለአካባቢው ሕዝብ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ሲያካፍሉ ቆዩ። ከዚያም ሐሙስ ጉዟቸውን ቀጠሉ፤ በማሮኒ ወንዝ ላይ ለአምስት ሰዓት ተኩል ተጉዘው ወደ አፓቱ መንደር ደረሱ።
ዘመቻው ከመጠናቀቁ በፊት ባለው ቀን የቡድኑ አባላት ማሩኖች የሚኖሩባቸውን በደኑ ውስጥ ያሉ መንደሮች ጎበኙ፤ ማሩን ተብለው የሚጠሩት፣ ጎረቤት አገር የሆነችው ሱሪናም በቅኝ ግዛት በተያዘችበት ወቅት ከአፍሪካ የመጡ ባሪያዎች ተወላጆች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮቹ ደኑ ውስጥ በተከሉት ትልቅ ድንኳን ሥር በሚደረግ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ነዋሪዎቹን በሙሉ ጋበዙ። ክሎድ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ሰዎች መምጣታቸውን ስናይ ልባችን በደስታ ተሞላ። የጋበዝናቸው በዚያው ዕለት ነበር።” ወደዚያ አካባቢ ሲሄድ የመጀመሪያው የሆነው ካርስተን “ሕይወት ማለት የአሁኑ ብቻ ነውን?” በሚል ርዕስ በኦካን ቋንቋ የሕዝብ ንግግር አቀረበ። ከተለያዩ መንደሮች የመጡ 91 ሰዎች በስብሰባው ላይ ተገኘተዋል።
“ድጋሚ ለመሄድ ዝግጁ ነን!”
በመጨረሻም የቡድኑ አባላት ወደ ሳን ለሬን ዱ ማሮኒ ተመለሱ። ሁሉም ተሳታፊዎች፣ ያነጋገሯቸው ሰዎች በሰጡት አዎንታዊ ምላሽ በጣም ተደስተው ነበር። በርካታ ጽሑፎችን ያበረከቱ ሲሆን ብዙ ቪዲዮዎችንም አሳይተዋል።
ሊዜት “በዚህ ዘመቻ በመካፈሌ ምን ያህል እንደተደሰትኩ ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል” ብላለች። ሲንዲ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “በድጋሚ የመሄድ አጋጣሚ ባገኝ በጣም ደስ ይለኛል። እንዲህ ያለውን ደስታ ያላጣጣመው ሰው ሊረዳው አይችልም!”
አንዳንዶቹ ተሳታፊዎች በድጋሚ ወደዚያ ለመሄድ ተነሳስተዋል። ሚካኤል “ድጋሚ ለመሄድ ዝግጁ ነን” ብሏል። ዊንስሊ ወደ ሳን ለሬን ዱ ማሮኒ ተዛውሮ በዚያ መኖር ጀምሯል። በ60ዎቹ ዕድሜ የሚገኙት ክሎድና ሊዜት ደግሞ በአፓቱ ለመኖር ወስነዋል።