በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት በድምፅ የተቀረጸ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት በድምፅ የተቀረጸ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ

“ትኩረት የሚስብ፣ በጥልቅ እንድናስብ የሚያደርግና ሕያው የሆነ።”

“የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን ሕያው የሚያደርግ።”

“የሚመስጥ! እስካሁን ከሰማኋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች ሁሉ ይበልጥ ሕያው የሆነ።”

እነዚህ አስተያየቶች በ​jw.org ላይ በድምፅ ተቀድቶ በእንግሊዝኛ የወጣውን የማቴዎስ መጽሐፍ አስመልክቶ ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በድምፅ መቅዳት የጀመሩት በ1978 ነው። ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በከፊልም ሆነ በሙሉ በ20 ቋንቋዎች በድምፅ ቀድተው አውጥተዋል።

የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም በ2013 መውጣቱ ሌላ የድምፅ ቅጂ ማዘጋጀት አስፈላጊ እንዲሆን አድርጓል። ሦስት አንባቢዎች ብቻ ከነበሩበት ከበፊቱ የድምፅ ቅጂ በተለየ አሁን የሚዘጋጀው የድምፅ ቅጂ ከ1,000 ለሚበልጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ለእያንዳንዳቸው የተለያየ ድምፅ ይጠቀማል።

የተለያዩ አንባቢዎችን መጠቀም አድማጮች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ ያሉትን ክንውኖች በዓይነ ሕሊናቸው እንዲስሉ ይረዳቸዋል። ቅጂው ተጨማሪ ድምፆችና ሙዚቃዎች የሚገቡበት ድራማዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ባይሆንም ታሪኮቹ ለሰዎች ሕያው ሆነው እንዲታዩ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።

በርካታ ሰዎች የሚሳተፉበት ሥራ ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ ማውጣት ይጠይቃል። በመጀመሪያ፣ ምርምር እንዲያደርጉ የተመደቡ ሰዎች በእያንዳንዱ ዘገባ ውስጥ ያሉት ተናጋሪዎች እነማን እንደሆኑ፣ በዘገባው ውስጥ ሊተላለፍ የተፈለገው ሐሳብ ምን እንደሆነና በምን ዓይነት ስሜት እንደተናገሩት ለማወቅ ምርምር ያደርጋሉ። ለምሳሌ አንድን ዘገባ የተናገረው አንድ ሐዋርያ ቢሆንና የተናጋሪው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ ባይጠቀስ መጠቀም ያለብን የየትኛውን ሐዋርያ ድምፅ ነው? ሐሳቡ ጥርጣሬን የሚገልጽ ከሆነ የቶማስን፣ ችኮላ የሚታይበት ከሆነ ደግሞ የጴጥሮስን ድምፅ መጠቀም ይቻል ይሆናል።

የተጠቀሰውን ባለታሪክ ዕድሜ መወሰንም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ ወጣት በነበረበት ወቅት ለተናገራቸው ነገሮች የወጣት ድምፅ በዕድሜ ገፍቶ እያለ ለተናገራቸው ነገሮች ደግሞ በዕድሜ የገፋ ሰው ድምፅ መጠቀም ያስፈልጋል።

በተጨማሪም ጥሩ አንባቢዎችን ማግኘት አስፈላጊ ነው። አብዛኞቹ አንባቢዎች የተመረጡት በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ከሚያገለግሉ ወንድሞች መካከል ነው። ለማንበብ በዕጩነት የሚቀርቡት፣ ከንቁ! መጽሔት ላይ የተመረጡ አንቀጾችን ተዘጋጅተው እንዲያነቡ ይደረጋል። በተጨማሪም እንደ ቁጣ፣ ሐዘን፣ ደስታ ወይም ተስፋ መቁረጥ ያሉ ስሜቶችን በትክክል መግለጽ ይችሉ እንደሆነ ለማወቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ አንዳንድ ዘገባዎች የተወሰኑ መስመሮችን ያነባሉ። ይህም የአንባቢዎቹን ችሎታ ለመገምገምና የትኛውን ዘገባ ቢያነቡ ይበልጥ ጥሩ እንደሚሆን ለመወሰን ይረዳል።

አንባቢዎቹ የሚያነቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከተሰጣቸው በኋላ ብሩክሊን፣ ፓተርሰን ወይም ዎልኪል ከሚገኙት ስቱዲዮዎች በአንዱ ይቀዳሉ። አለማማጁ አንባቢዎቹ ተገቢውን የድምፅ ቃና መጠቀማቸውን እንዲሁም የድምፅ ቅጂውን ጥራት ይከታተላል። አለማማጁና አንባቢዎቹ ለዚህ ዓላማ ተብሎ የተዘጋጀውን ጽሑፍ ይጠቀማሉ፤ ይህ ጽሑፍ፣ አንባቢዎቹ ቆም የሚሉበትንና ማጥበቅ የሚኖርባቸውን ቦታዎች የሚጠቁሙ መመሪያዎች አሉት። አለማማጁ ከዚህ በፊት የተዘጋጀውን የአዲስ ዓለም ትርጉም የድምፅ ቅጂ እንደ መመሪያ አድርጎ ይከተላል።

ቅጂው በሚከናወንበት ወቅት በተቀዳው ድምፅ ላይ አንዳንድ እርማቶች ይደረጋሉ። ጥራት ያለው ቅጂ ለማዘጋጀት አንዳንድ ጊዜ በተለያዩ ጊዜ የተቀዱ ቃላትን ወይም ሐረጎችን አንድ ላይ መገጣጠም ሊያስፈልግ ይችላል።

በ2013 ተሻሽሎ የወጣውን አዲስ ዓለም ትርጉም ሙሉውን ቅጂ ለማዘጋጀት ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ቅጂ እንዳለቀ jw.org ላይ እንዲወጣ ይደረጋል፤ በዚህ ወቅት “የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት” በሚለው ገጽ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆነው መጽሐፍ ስም አጠገብ የኦዲዮ ምልክት ይታያል።