ጽሑፎቻችንን ወደ ኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ መተርጎም
በካናዳ ምሥራቃዊ ክፍል ባሉ ፈረንሳይኛ በስፋት የሚነገርባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አብዛኞቹ መስማት የተሳናቸው ሰዎች የሚጠቀሙት የኪዩቤክ ምልክት ቋንቋን ነው። a በዚህ የምልክት ቋንቋ የሚጠቀሙት 6,000 የሚያክሉ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ብቻ ስለሆኑ በኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ የሚገኙ ነገሮች ቁጥር አነስተኛ ነው። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያውቁ የመርዳት ፍላጎት ስላላቸው ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን በነፃ የሚሰራጩ ጽሑፎች በኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ ለማዘጋጀት የሚያደርጉትን ጥረት አፋፍመዋል።
ጽሑፎቻችንን ወደ ኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ ለመተርጎም የሚደረገው ጥረት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለመረዳት የማርሴልን ታሪክ እንመልከት። ማርሴል የካናዳ ግዛት በሆነችው በኪዩቤክ በ1941 ተወለደ። የሁለት ዓመት ልጅ ሳለ በማጅራት ገትር በሽታ በመያዙ የመስማት ችሎታውን አጣ። ማርሴል እንዲህ ብሏል፦ “በዘጠኝ ዓመቴ መስማት ለተሳናቸው ልጆች ወደተዘጋጀ ትምህርት ቤት ገባሁ፤ በዚያም የኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ ተማርኩ። መሠረታዊ ምልክት ቋንቋን ለማስተማር የተዘጋጁ አንዳንድ መጻሕፍት ቢኖሩም በምልክት ቋንቋ የተዘጋጀ ምንም ጽሑፍ አልነበረም።”
በኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎችን ማዘጋጀት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ማርሴል ምክንያቱን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “መስማት የተሳናቸው ሰዎች ብዙም በማይገባቸው ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ ለመረዳት ከሚታገሉ ይልቅ ሙሉ በሙሉ በሚረዱት ቋንቋ የተዘጋጀ መረጃ ቢያገኙ ደስ ይላቸዋል። ጽሑፎች በኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ ባይዘጋጁ ኖሮ በንግግር ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ ለመጠቀም እንገደድ ነበር፤ በንግግር ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎች ላይ ደግሞ ብዙ የማይገቡን ነገሮች አሉ!”
የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ማርሴል ያሉ የኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ የሚጠቀሙ መስማት የተሳናቸው ሰዎችን ለመርዳት፣ በኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ የተዘጋጀውን የመጀመሪያ ጽሑፍ በ2005 አወጡ። በቅርቡ ደግሞ በሞንትሪያል፣ ኪዩቤክ የሚገኘውን የትርጉም ቢሯቸውን አስፋፍተዋል። በዚህ ቢሮ ውስጥ ሙሉ ጊዜ የሚሠሩ ሰባት ሰዎችና በሳምንት ውስጥ የተወሰኑ ቀናት የሚሠሩ ከአሥር በላይ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች በሦስት የትርጉም ቡድኖች የተደራጁ ሲሆን በኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎችን ለማዘጋጀት አስፈላጊው መሣሪያ ሁሉ የተሟላላቸው ሁለት ስቱዲዮዎችን ይጠቀማሉ።
የኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ ተጠቃሚ የሆኑት ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጇቸው ጽሑፎች ያላቸውን ጥራት ያደንቃሉ። አሶሲያሲዮን ደ ሱር ደ ሌስትሪ የተባለው በኪዩቤክ ለሚገኙ መስማት የተሳናቸው ሰዎች እርዳታ የሚሰጥ ድርጅት ምክትል ኃላፊ የሆኑት ስቴፈን ዣክ እንዲህ ብለዋል፦ “የቪዲዮ ፕሮግራሞቹ ከፍተኛ ጥራት አላቸው። ሰዎቹ የሚጠቀሙባቸው ምልክቶች ግልጽ ናቸው፤ በፊታቸው ላይ የሚታዩት መግለጫዎችም በጣም ይማርካሉ። ሰዎቹ ያላቸውን ጥሩ አለባበስም አደንቃለሁ።”
በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በሳምንታዊ ስብሰባዎቻቸው ላይ የሚጠቀሙበት መጠበቂያ ግንብ የተባለው መጽሔት በአሁኑ ጊዜ በኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ ይዘጋጃል፤ ኪዩቤክ ውስጥ በዚህ ቋንቋ የሚመሩ ሰባት ጉባኤዎችና ቡድኖች ያሉ ሲሆን በእነዚህ ጉባኤዎችና ቡድኖች ውስጥ የሚሰበሰቡት 220 የይሖዋ ምሥክሮች እንዲሁም ሌሎች ሰዎች በዚህ መጽሔት ይጠቀማሉ። b በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥራቸው በየጊዜው እያደገ የመጣ ቪዲዮዎችን በኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ አዘጋጅተው ኢንተርኔት ላይ ያወጣሉ፤ ከእነዚህ ቪዲዮዎች መካከል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ አስደሳች መዝሙሮች ይገኙበታል።
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ማርሴል በኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ የሚዘጋጁ ጽሑፎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነው። በተለይ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያዘጋጇቸው ጽሑፎች ለየት ያለ አድናቆት አለው። እንዲህ ብሏል፦ “jw.org ላይ በኪዩቤክ ምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ በርካታ ቪዲዮዎች መኖራቸው ትልቅ በረከት ነው። በቋንቋዬ የተዘጋጁ ብዙ ነገሮች መኖራቸውን ሳይ በጣም እደሰታለሁ!”