በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የጽሑፉን መልእክት የሚያዳብሩ ፎቶግራፎች

የጽሑፉን መልእክት የሚያዳብሩ ፎቶግራፎች

ፎቶግራፍ አንሺዎቻችን ጽሑፎቻችንን ይበልጥ ማራኪ የሚያደርጉና የጽሑፉን መልእክት የሚያዳብሩ ፎቶግራፎችን የሚያነሱት እንዴት ነው? ዝርዝር ሂደቱን ለመመልከት የመስከረም 2015 ንቁ! ሽፋን ላይ የሚገኘው ፎቶግራፍ የተዘጋጀበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። a

  • ዲዛይን፦ በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ውስጥ ባለው የሥነ ጥበብ ክፍል ውስጥ የሚሠሩ ሠዓሊዎች “ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ” የሚለውን ርዕስ ካነበቡ በኋላ የጽሑፉን መልእክት የሚገልጹ ንድፎችን አዘጋጁ። ከዚያም እነዚህን ንድፎች ለበላይ አካሉ የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ አቀረቡ፤ የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴውም ከእነዚህ መካከል ወደ ፎቶግራፍ እንዲቀየር የሚፈልገውን መረጠ።

    የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴው እንዲመለከታቸው ለምርጫ የቀረቡ በመጽሔቱ ሽፋን ላይ የሚወጡ ሥዕሎች

  • ቦታ፦ ፎቶግራፍ አንሺዎቹ፣ ፎቶግራፎቹን በቀጥታ ባንክ ቤት ሄዶ ከማንሳት ይልቅ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ውስጥ ከሚገኙ የእንግዳ መቆያ ቦታዎች አንዱን ባንክ ቤት አስመስሎ ተጠቀመበት። b

  • ተዋንያን፦ ፎቶግራፍ እንዲነሱ የተመረጡት ሰዎች በሙሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሲሆኑ በአንድ ትልቅ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ባንክ የሚኖሩትን ደንበኞች ሊወክሉ የሚችሉ ናቸው። የተመሳሳይ ሰዎች ፎቶግራፍ በጽሑፎቻችን ላይ በተደጋጋሚ እንዳይወጣ በፎቶግራፎቹ ውስጥ የተካተቱ ሰዎች ዝርዝር ተመዝግቦ ይቀመጣል።

  • ቁሳቁሶች፦ የሥነ ጥበብ ክፍሉ ባንኩ የሚገኘው ከዩናይትድ ስቴትስ ውጪ እንደሆነ ለማስመሰል የውጭ ምንዛሪ ተጠቅሟል። ፎቶግራፍ አንሺዎቹ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ስፍራው በተቻለ መጠን ባንክ እንዲመስል ለማድረግ ጥረዋል። ክሬግ የተባለ ፎቶግራፍ አንሺ “ሁሉ ነገር ጥንቃቄ ይጠይቃል” በማለት ተናግሯል።

  • ልብስና ሜካፕ፦ ባንክ ቤት ውስጥ በተነሳው ፎቶግራፍ ላይ የሚታዩት ሰዎች የተጠቀሙት የራሳቸውን ልብስ ነው። ነገር ግን ፎቶግራፉ የድሮ ዘመን አለባበስ ወይም የደንብ ልብስ መልበስ የሚጠይቅ ከሆነ የሥነ ጥበብ ክፍሉ በዚህ ላይ ጥናት በማድረግ አስፈላጊውን ልብስ ያዘጋጃል። ሜካፕ አርቲስቶቹ ከፎቶግራፉ መቼትና አውድ ጋር የሚስማማ ሜካፕ ይጠቀማሉ። ክሬግ እንዲህ ብሏል፦ “በአሁኑ ጊዜ የሚነሱ ፎቶግራፎች በጣም ጥራት ስላላቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ትንሽ ስህተት እንኳ በፎቶግራፉ አማካኝነት እንዲተላለፍ የተፈለገውን መልእክት ሊያዛባው ይችላል።”

  • ፎቶ ማንሳት፦ ፎቶግራፍ አንሺዎቹ በባንኩ ውስጥ ያለው ብርሃን ፎቶው በቀን የተነሳ መሆኑን የሚያሳይ እንዲሆን አደረጉ። እያንዳንዱ ፎቶ በሚነሳበት ጊዜ ፎቶግራፍ አንሺዎቹ ብርሃኑ የተፈለገው (የፀሐይ፣ የጨረቃ ወይም ሰው ሠራሽ ብርሃን) ዓይነት መሆኑን፣ ፎቶግራፉ በሚነሳበት ቦታ ላይ ካለው ብርሃን ጋር የሚስማማ መሆኑንና በፎቶግራፉ ለማስተላለፍ ከተፈለገው መልእክት ጋር የሚጣጣም መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው። ክሬግ እንዲህ ብሏል፦ “ፎቶግራፍ እንደ ቪዲዮ አይደለም፤ በአንድ ፎቶግራፍ አማካኝነት ትክክለኛውን ስሜት ማስተላለፍ ይጠይቃል፤ ለዚህ ደግሞ ትክክለኛ የብርሃን ቅንብር ያስፈልጋል።”

  • ኤዲት ማድረግ፦ በኋላ ላይ ኤዲት የሚያደርጉት ሰዎች የገንዘብ ኖቱ ደብዘዝ እንዲል አደረጉ፤ ይህም አንባቢዎች ገንዘቡ የየት አገር ኖት እንደሆነ ለማወቅ ከመሞከር ይልቅ ፎቶግራፉ ውስጥ ባሉት ሰዎች ላይ እንዲያተኩሩ ይረዳል። የበሩና የመስኮቱ ፍሬም ቀለም ቀይ ቢሆንም ኤዲት በሚደረግበት ጊዜ ወደ አረንጓዴ ተቀይሯል፤ እንዲህ የተደረገው ከሽፋኑ አጠቃላይ ቀለም ጋር አብሮ እንዲሄድ ሲባል ነው።

ፎቶግራፍ የማንሳቱ ሥራ ከፓተርሰን በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ይካሄዳል፤ ከእነዚህ መካከል ማላዊ፣ ሜክሲኮ፣ ብራዚል፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ኮሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጀርመንና ጃፓን የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡ ፎቶዎችን የሚያነሱ ፎቶግራፍ አንሺዎች አሏቸው፤ ስለዚህ እነዚህ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ፎቶግራፎችን እንዲልኩ ሊጠየቁ ይችላሉ። በፓተርሰን የሚገኘው የሥነ ጥበብ ክፍል በየወሩ 2,500 ገደማ አዳዲስ ፎቶግራፎችን በስብስቡ ላይ ይጨምራል። ብዙዎቹ ፎቶግራፎች በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ታትመው ይወጣሉ፤ በ2015 የእነዚህ መጽሔቶች የአንድ ወር እትም በድምሩ ከ115 ሚሊዮን በላይ ቅጂዎች ተሰራጭቷል። ስለምናከናውነው ሥራ ይበልጥ ለማወቅ በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክም ሆነ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎቻችንን መካከል አመቺ ሆኖ ያገኘኸውን እንድትጎበኝ እንጋብዝሃለን

አንድ ወንድም በአገልግሎት ላይ መጽሔት ሲያበረክት

a ለሽፋን የሚሆን ፎቶግራፍ በሚፈለግበት ጊዜ ብዙ አማራጭ ፎቶዎች ይነሳሉ። ሆኖም በወቅቱ ጥቅም ላይ ያልዋሉት ፎቶግራፎች በፎቶዎች ስብስብ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን ወደፊት ሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ።

b ፎቶግራፉ የሚነሳው በከተማ መንገድ ላይ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ የሥነ ጥበብ ክፍሉ ምን ያህል ሰው በሥራው ላይ እንደሚካፈል፣ ሰዎቹ የሚጠቀሙበትን መሣሪያ ብዛትና ፎቶውን ለማንሳት የሚጠቀሙበትን የመብራት ዓይነት በመግለጽ ከባለሥልጣናት ፈቃድ ይጠይቃል።