በጣሊያን የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ጎረቤቶቻቸውን ረዱ
በኅዳር 2016 መገባደጃ አካባቢ በሰሜናዊ ጣሊያን በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ከሞንካሊዬሪ ከተማ በስተ ደቡብ የሚገኙ አንዳንድ መንደሮች በውኃ ተጥለቅልቀው ነበር። በአንዳንድ ቦታዎች ውኃው ከግማሽ ሜትር በላይ ጥልቀት ነበረው። አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው “ውኃው ያስቀረው አንድም ነገር አልነበረም።” አደጋው ከደረሰ በኋላ የአካባቢው ባለሥልጣናት 1,500 ገደማ የሚሆኑ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አድርገው ነበር። የነፍስ አድን ሠራተኞች አፋጣኝ እርምጃ በመውሰዳቸው በአደጋው ምክንያት የሞተ አንድም ሰው አልነበረም። ሆኖም በርካታ ቤተሰቦች ንብረታቸውን አጥተዋል።
የእርዳታ ቡድኑ ድጋፍ ሰጠ
በአካባቢው የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ወዲያውኑ በቡድን ተደራጅተው እርዳታ መስጠት ጀመሩ። ጎርፉ ያመጣውን ጭቃና ፍርስራሽ ከመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ዝቀው በማውጣት እንዲሁም በድጋሚ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ዕቃዎችን በመለየት በአደጋው ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች ረድተዋል። አንድ ቡድን የተለያዩ ዕቃዎችንና ትኩስ ምግብ ይዞ በመሄድ ላይ ሳለ መንገድ ስለተዘጋበት ማለፍ አልቻለም ነበር፤ ሆኖም የአካባቢው ባለሥልጣናት ቡድኑ ማለፍና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ቤተሰቦች መርዳት እንዲችል እገዛ አድርገዋል። ፈቃደኛ ሠራተኞቹ እንደ እነሱ የይሖዋ ምሥክሮች ለሆኑትም ሆነ የሌላ እምነት ተከታይ ለሆኑ ጎረቤቶቻቸው እርዳታ ሰጥተዋል።
ለምሳሌ ያህል፣ የአንድ መኖሪያ ሕንፃ ምድር ቤት ሙሉ በሙሉ በጎርፍ ተጥለቅልቆ ነበር። የነፍስ አድን ሠራተኞች ውኃውን ስበው ካወጡ በኋላ ብዙ አባላትን ያቀፈ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን አንቶኒዮ የተባለን የይሖዋ ምሥክርና ቤተሰቡን ከቤታቸው ፍርስራሾችን በማጽዳት ረዷቸው። በመቀጠልም ፈቃደኛ ሠራተኞቹ በሕንፃው ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ነዋሪዎችንም ረዱ። የቡድኑ አባላት ጎን ለጎን ቆመው ቆሻሻውን በመቀባበል በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በምድር ቤቱ ያሉትን ክፍሎች በሙሉ አጽድተው ጨረሱ። ሁሉም ሰው ቡድኑ ላደረገው እርዳታ ከፍተኛ አድናቆት አሳይቷል። ከነዋሪዎቹ አንዷ የሆነችው ቪቪያና ዓይኖቿ በእንባ ተሞልተው ወደ አንቶኒዮ ሚስት በመሄድ “ወንድሞችሽን በጣም አመስግኚልን፤ በጣም ልዩ ሰዎች ናችሁ!” ብላታለች።
ጎርፉ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰበት አንድ መንደር ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች በቡድን የተደራጁ የይሖዋ ምሥክሮች አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች ሲረዱ ተመልክተው ነበር። አንዳንዶቹ ባዩት ነገር ልባቸው በጣም ስለተነካ እርዳታ የሚሰጡትን ሠራተኞች ለማገዝ የተነሳሱ ሲሆን እነዚህ ሰዎች የቡድኑ መሪ የሚሰጣቸውን መመሪያ በደስታ ተቀብለው ይሠሩ ነበር።
ለተደረገላቸው “በዋጋ የማይተመን እርዳታ” አድናቆታቸውን ገልጸዋል
አንድ ሰው ቤቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን መኪና ማቆሚያውም በጭቃ ተሞልቶ ነበር። ይህ ግለሰብ ስምንት የይሖዋ ምሥክሮች ያለምንም እረፍት ለአራት ሰዓት ያህል ከቤቱ ውስጥ ፍርስራሾችን ለማውጣት መሥራታቸው በጣም አስገረመው። አድናቆቱን ለመግለጽ አንዳንዶቹን ሠራተኞች ያቀፋቸው ከመሆኑም ሌላ ለሰጡት “በዋጋ የማይተመን እርዳታ” ያለውን አመስጋኝነት የሚገልጽ መልእክት በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ አውጥቷል።
አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ በርካታ ጎረቤቶቻችንን የረዳን ሲሆን ብዙዎቹ በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አረጋውያን ነበሩ። አንዳንዶቹ ላከናወንነው ሥራ አድናቆታቸውን ሲገልጹ ዓይናቸው እንባ ያቀር ነበር።” በአካባቢው በሚገኝ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ አንድ ጎረቤት፣ የይሖዋ ምሥክሮች ላደረጉት እርዳታ ያለውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጿል፤ አክሎም “የተለያየ ሃይማኖት ያለን ብንሆንም እርስ በርስ መረዳዳታችን በጣም ያስደስታል” ብሏል። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ “ብዙዎች እሁድ ጠዋት እየሄዳችሁ ሰዎችን እንደምታነጋግሩ ብቻ እንጂ እንዲህ ያለ እርዳታ እንደምትሰጡ አለማወቃቸው ያሳዝናል” በማለት ተናግሯል።