በፈረንሳይ የተካሄደ ለየት ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ አውደ ርዕይ
በሰሜን ፈረንሳይ በምትገኘው በሩዋ ከተማ በ2014 በተካሄደው ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች “መጽሐፍ ቅዱስ—ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ” የሚል ስያሜ የተሰጠውን አንድ ትኩረት የሚስብ ክፍል ጎብኝተው ነበር።
ከክፍሉ ውጭ በተሰቀሉ ስክሪኖች ላይ ጥንታዊ ስለሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች የሚያሳይ ቪዲዮ ተከፍቶ ነበር፤ ይህ ቪዲዮ የብዙ ጎብኚዎችን ትኩረት ስቧል። ጎብኚዎቹ ውስጥ ከገቡ በኋላ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስለያዘው ጠቃሚ ምክር፣ ከታሪክ እና ከሳይንስ አንጻር ትክክለኛ ስለ መሆኑ እንዲሁም በስፋት ስለ መሰራጨቱ የሚገልጽ መረጃ ማግኘት ችለዋል።
በተጨማሪም ጎብኚዎቹ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ተጠብቆ ሊቆይ የቻለውና በዛሬው ጊዜ በተለያዩ የሕትመት ውጤቶችና ኤሌክትሮኒክ ፎርማቶች አማካኝነት በቢሊዮን የሚቆጠሩ አንባቢዎች እጅ ሊገባ የቻለው እንዴት እንደሆነ ማየት ችለዋል። ከዚህም ሌላ አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ በነፃ አግኝተዋል፤ ይህ ትርጉም በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ሲሆን ከ120 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉሟል።
ብዙ ጎብኚዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ በሕዝቡ እጅ እንዲገባ ላደረጉት ጥረት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። ለወጣቶች ማኅበራዊ አገልግሎት የምትሰጥ አንዲት ሴት ከተወሰኑ ወጣቶች ጋር ሆና አውደ ርዕዩን ጎብኝታ ነበር፤ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥታለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስ የሁላችንም ቅርስ ነው። ሕያው የሆነ መጽሐፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ባነበብኩ ቁጥር ለሚያጋጥሙኝ ችግሮች መፍትሔ የሚሆን ሐሳብ አገኛለሁ።”
አንዲት የ60 ዓመት ሴት፣ መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ማግኘት በመቻላቸው በጣም ተገርመው ነበር። እኚህ ሴት “ሁላችንም እንደገና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ መጀመር አለብን፤ ምክንያቱም ሁላችንም ያስፈልገናል!” በማለት ተናግረዋል።