በዎርዊክ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አብሮ መሥራት
በዎርዊክ የግንባታ ሥራ የሚሳተፉ ሰዎች የሚያሳዩት የፈቃደኝነት መንፈስ ብዙ ሰዎችን አስደንቋል። አሳንሰሮቹን የገጠመው ድርጅት ሥራ አስኪያጅ በግንባታው ሥራ ለሚካፈል አንድ ሰው እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ቡድናችሁ እያከናወነ ያለው ሥራ በጣም አስደናቂ ነው። በዛሬው ጊዜ ጊዜያቸውን በፈቃደኝነት የሚሰጡ ብዙ ሰዎች የሉም።”
ይህን ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሰዎች በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ እየተገነባ ባለው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የግንባታ ሥራ የሚካፈሉት አብዛኞቹ ሰዎች ፈቃደኛ ሠራተኞች እንደሆኑ ሲሰሙ፣ በአካባቢው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ሄደው እንደሚሠሩ አስበው ነበር። በፕሮጀክቱ ላይ ለወራት ብሎም ለዓመታት ለመካፈል ሲሉ የግል ሥራቸውን ትተው ከመላው የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ ሰዎች መሆናቸውን ሲገነዘቡ በጣም ተገርመው ነበር።
እስከ 2015 መጨረሻ ድረስ 23,000 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክር ፈቃደኛ ሠራተኞች ከዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል ቤተሰብ አባላት ጋር በመሆን በዎርዊክ ግንባታ ላይ ተካፍለዋል። ከእነዚህ በተጨማሪ ፕሮጀክቱ በተመደበለት ጊዜ መጠናቀቅ እንዲችል 750 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ የግንባታ ሠራተኞችም በሥራው ተካፍለዋል። ከእነዚህ የግንባታ ባለሙያዎች መካከል ብዙዎቹ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በቅርበት መሥራታቸው ለይሖዋ ምሥክሮች አድናቆት እንዲያድርባቸው አድርጓል።
አስደሳች የሥራ ቦታ
መስኮትና ግድግዳ የሚሠራ አንድ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በዚህ ፕሮጀክት የተካፈሉት ሠራተኞቻችን በሙሉ አብረዋቸው ይሠሩ የነበሩት ሰዎች በሚያሳዩት ባሕርይ ተደንቀዋል። ብዙዎቻችን በዚህ ፕሮጀክት መካፈል የምንፈልገው በዚህ ምክንያት ነው።”
ሌላ ድርጅት ደግሞ የመኖሪያ ሕንፃዎቹን መዋቅር የሚገነቡ ሠራተኞች አቅርቦ ነበር። ድርጅቱ ኮንትራቱን ሲያጠናቅቅ ከሠራተኞቹ መካከል ሦስቱ ከዎርዊክ ግንባታ ቦታ መልቀቅ አልፈለጉም። በዚህም ምክንያት መሥሪያ ቤታቸውን በመልቀቅ በዎርዊክ ግንባታ ቦታ የሚሠራ ሌላ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው መሥራት ጀመሩ።
የይሖዋ ምሥክሮቹ የሚያንጸባርቋቸው ክርስቲያናዊ ባሕርያት በአንዳንድ ሠራተኞች ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ለምሳሌ፣ አንድ ሰው ለሕንፃዎች መሠረት በሚጥል ድርጅት ተቀጥሮ ይሠራ ነበር። በዎርዊክ መሥራት ከጀመረ ከጥቂት ወራት በኋላ ሚስቱ በባሕርይውና በአነጋገሩ ረገድ ትልቅ ለውጥ እንዳደረገ ማስተዋል ችላ ነበር። “የማላውቀው አዲስ ሰው ነው የሆነብኝ!” በማለት በደስታ ተናግራለች።
‘የይሖዋ ምሥክር የሆኑት ሴቶች እንኳ ሥራ ይገባሉ’
በግንባታ ቦታው ላይ ከሚሠሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ብዙዎቹ ሴቶች ነበሩ። ሥራቸው አውቶቡስ መንዳት፣ ክፍሎችን ማጽዳትና ጸሐፊነት ብቻ ሳይሆን በግንባታ ቦታው ያለውን የትራፊክ ፍሰት ይቆጣጠራሉ፤ ከባድ ማሽኖችን ያንቀሳቅሳሉ፤ ፋይበር ኦፕቲክ ሽቦዎችን ይቀጥላሉ፤ የውኃ መስመሮች ላይ ሙቀትን ጠብቆ የሚያቆይ ሽፋን ያለብሳሉ፤ ተሠርተው የተጠናቀቁ ግድግዳዎችን ይገጥማሉ፤ የቧንቧ መስመሮችን ይዘረጋሉ እንዲሁም አርማታ ይሞላሉ። ሥራቸውን በትጋት ያከናውናሉ።
ጣሪያ የማልበስ ሥራ የሚሠራ አንድ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ ሰው አንዳንድ ባልና ሚስቶች ከአውቶቡሶቹ ወርደው ወደ ሥራ ሲሄዱ እጅ ለእጅ እንደሚያያዙ አስተዋለ። ይህ ልቡን ነካው። በተጨማሪም ሴቶቹ በፕሮጀክቱ ላይ በትጋት ሲሠሩ ተመለከተ። እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ሚስቶቹ እንዲሁ ባሎቻቸውን ለማጀብ የመጡ ይመስላችሁ ይሆናል። ነገር ግን እነሱም በሚገባ ይሠራሉ! ኒው ዮርክ ሲቲ በሚገኙ የተለያዩ የግንባታ ቦታዎች ላይ ሠርቻለሁ፤ ሆኖም ይህን የመሰለ ነገር አይቼ አላውቅም።”
የ2014/2015 የክረምት ወቅት ከወትሮው በተለየ መልኩ ከባድ ነበር፤ በዚህ ኃይለኛ ቅዝቃዜ ውጪ ከመሥራት ይልቅ ቤት መዋል ያሰኛል። የግንባታ ሥራውን ይቆጣጠር የነበረው ጄረሚ የተባለ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “የአንድ ድርጅት የሠራተኞች ተቆጣጣሪ በጣም ብርድ በሚሆንባቸው ጊዜያት ‘ነገ ሴቶች ሠራተኞቻችሁ ሥራ ይገባሉ?’ በማለት ይጠይቀኝ ነበር።”
“‘አዎ።’
“‘ውጪ ቆመው ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናብሩትም ጭምር?’
“‘አዎ።’
“ከዚያም ወንዶች የሆኑ ሠራተኞቹን፣ የይሖዋ ምሥክር የሆኑት ሴቶች እንኳ ሥራ ስለሚገቡ እነሱም ሥራ መግባት እንዳለባቸው ይነግራቸው እንደነበረ ከጊዜ በኋላ ተናግሯል!”
የአውቶቡስ አሽከርካሪዎች ሥራቸውን ወደውታል
ከ35 የሚበልጡ የአውቶቡስ አሽከርካሪዎች በዎርዊክ የሚሠሩትን ፈቃደኛ ሠራተኞች ከመኖሪያ ቦታቸው ወደ ግንባታ ቦታው እንዲያመላልሱ ተቀጥረው ነበር።
በአንድ ወቅት፣ አንዱ የአውቶቡስ አሽከርካሪ መንገድ ከመጀመራቸው በፊት ወደ ተሳፋሪዎቹ ዞሮ በመቆም እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “እናንተ የይሖዋ ምሥክሮችን የማመላለሱን ሥራ በጣም ወድጄዋለሁ። እባካችሁ ለአለቃዬ ኢሜይል በመጻፍ ከዚህ ሥራዬ እንዳይቀይረኝ ጠይቁልኝ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ከእናንተ ብዙ ተምሬአለሁ። ከእናንተ ጋር ከመገናኘቴ በፊት የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ወይም ምድር ገነት እንደምትሆን አላውቅም ነበር። አሁን ሞትን አልፈራም። ይህን የመሰለ አጋጣሚ ማግኘቴ በጣም አስደስቶኛል። በሚቀጥለው ጊዜ እረፍት ሲኖረኝ ወደ መንግሥት አዳራሻችሁ እንደምመጣ አትጠራጠሩ።”
በዎርዊክ ትሠራ የነበረችው ዳሚያና የተባለች የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ቀን ወደ አውቶቡሱ ከገባን በኋላ አሽከርካሪው ሊነግረን የሚፈልገው ነገር እንዳለው ተናገረ። በኒው ዮርክ በሚገኙ የተለያዩ የግንባታ ቦታዎች የሚሠሩ 4,000 የይሖዋ ምሥክሮችን ሲያመላልስ እንደቆየ ተናገረ። ከዚያም ‘የባህርይ ልዩነት መኖሩ የማይቀር ነገር ነው። እናንተ ግን ልዩነቶች ቢኖሯችሁም ተስማምታችሁና ተባብራችሁ ትሠራላችሁ። ይህ በጣም ደስ የሚል ነገር ነው’ ብሏል። በተጨማሪም ከእኛ ጋር ማውራት እንደሚያስደስተው ተናግሯል።
ተናግሮ ሲጨርስ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ‘መዝሙር ስንዘምርስ ደስ ይልሃል?’ ብላ ጠየቀችው።
ከት ብሎ ከሳቀ በኋላ ‘አዎ! ከመዝሙር 134 እንጀምር?’ በማለት መለሰ።” a