የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ136ኛው ክፍል የምረቃ ሥነ ሥርዓት
የጊልያድ ትምህርት ቤት የ136ኛው ክፍል ተማሪዎች፣ ለአምስት ወራት የተሰጣቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በትጋት ሲከታተሉ ቆይተው ቅዳሜ መጋቢት 8, 2014 ተመረቁ። በዚህ ትምህርት ቤት የተካፈሉት ተሞክሮ ያካበቱ የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎታቸው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑና የእምነት አጋሮቻቸውን እምነት ለማጠናከር የሚረዳ ትምህርት ቀስመዋል። በጠቅላላው 11,548 ሰዎች የምረቃ ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። ይህም በኒው ዮርክ፣ ፓተርሰን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የትምህርት ማዕከል በአካል የተገኙትንና በካናዳ፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በጃማይካና በፖርቶ ሪኮ ፕሮግራሙን በቪዲዮ አማካኝነት የተከታተሉትን ይጨምራል።
“ይህ አስተሳሰብ በእናንተም ዘንድ ይኑር።” የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባልና የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የሆነው ዴቪድ ስፕሌን “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ይህ አስተሳሰብ በእናንተም ዘንድ ይኑር” በሚለው በፊልጵስዩስ 2:5-7 ላይ ተመርኩዞ የመክፈቻ ንግግሩን አቀረበ። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ሥልጣን ፈላጊ ሰው አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ሕይወቱን አምላክ የሰጠውን ሥራ በትሕትና ለማከናወን ተጠቅሞበታል።
ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ዲያብሎስ ያቀረበለትን እያንዳንዱን ፈተና ውድቅ ለማድረግ ሙሴ ለእስራኤላውያን ከተናገረው ሐሳብ ላይ በመጥቀስ “ተብሎ ተጽፏል” ይል ነበር። (ማቴዎስ 4:4, 7, 10፤ ዘዳግም 6:13, 16፤ 8:3) ኢየሱስ የአምላክ ቅቡዕ ልጅ እንደመሆኑ መጠን በራሱ ሥልጣን መናገር ይችል የነበረ ቢሆንም በትሕትና ሙሴ ያከናወነውን ሥራ እንደሚያደንቅ አሳይቷል። እኛም ሌሎች ላላቸው ችሎታ እውቅና መስጠትና እነሱን ከልብ ማመስገን ይኖርብናል።
በተጨማሪም ወንድም ስፕሌን ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የሥልጠና ጊዜ መደምደሚያ ላይ ትክክለኛ አስተሳሰብ እንደነበረው ያሳየው እንዴት እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ “እንድሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርኩህ። ስለዚህ አባት ሆይ፣ ዓለም ከመመሥረቱ በፊት በጎንህ ሆኜ በነበረኝ ክብር አሁንም በጎንህ አድርገህ አክብረኝ” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 17:4, 5) ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ ተጨማሪ መብት እንዲሰጠው አልጠየቀም። ብቸኛ ልመናው ወደ ሰማይ ተመልሶ በሚሄድበት ጊዜ ወደ ቀድሞ ቦታው እንዲመለስ ወይም ‘የነበረውን ሥራ መልሶ እንዲያገኝ’ ነበር። በተመሳሳይም የጊልያድ ምሩቃን ትኩረት ማድረግ ያለባቸው መብት በማግኘት ላይ ሳይሆን በሚያከናውኑት ሥራ ላይ መሆን አለበት፤ ወደ አገልግሎት ምድባቸው ሲመለሱ ተጨማሪ መብቶችን ባያገኙ እንኳ በተሰጣቸው ሥራ በመርካት ኢየሱስን ሊመስሉት ይገባል።
“በምትከፍሉት መሥዋዕት አትቆጩ።” የበላይ አካሉ የትምህርት ኮሚቴ ረዳት የሆነው ዊሊያም ማሌንፎንት ተማሪዎቹ ሐዋርያው ጳውሎስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ረገድ የተወውን ምሳሌ እንዲከተሉ አበረታታቸው። ጳውሎስ ለአምላክ አገልግሎት ሲል ትቶ የመጣቸውን ነገሮች ከመመልከት ይልቅ “ከኋላዬ ያሉትን ነገሮች እየረሳሁ ከፊቴ ወዳሉት ነገሮች እንጠራራለሁ” ብሏል።—ፊልጵስዩስ 3:13, 14
ተማሪዎቹ በሚከፍሉት መሥዋዕት ባለመቆጨት የጥንቶቹንም ሆነ የዘመናችንን የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ሊመስሏቸው ይችላሉ። ወንድም ማሌንፎንት ይሖዋን በልጅነቷ ማገልገል የጀመረችውን ክላራ ገርበር ሞየርን ጠቀሰ። እንዲህ በማለት ጽፋ ነበር፦ “ከ80 ለሚበልጡ ዓመታት ለአምላክ ያቀረብኩትን የሙሉ ልብ አገልግሎት መለስ ብዬ ሳስበው ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም፤ ይህ ምንኛ ታላቅ መብት ነው! እንደገና ተመልሼ መኖር ብችል የምኖረው በዚያው መልክ ነበር።”
“መንግሥቱን ከመላእክት ጋር እንደ መላእክት መስበክ።” የበላይ አካል አባል የሆነው ጌሪት ሎሽ ተማሪዎቹ፣ ሰባኪዎች የሚያገኟቸውን ሁለት ልዩ መብቶች እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። አንደኛ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መላእክትን” ለማመልከት የተሠራባቸው የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት “መልእክተኛ” ተብለውም ሊተረጎሙ ስለሚችሉ ተማሪዎቹ የመንግሥቱን ምሥራች መልእክት ለሰዎች በሚያደርሱበት ጊዜ እንደ አምላክ መላእክት ሆነው ያገለግላሉ። ሁለተኛ፣ ደቀ መዝሙሩ ፊልጶስ እንዳደረገው ተማሪዎቹ ምሥራቹን የሚሰብኩት መንፈሳዊ ፍጥረታት በሆኑት በመላእክት እየተመሩ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 8:26-35
ከዚያም ወንድም ሎሽ የይሖዋ ምሥክሮች በመንግሥቱ ስብከት ሥራቸው ላይ ያጋጠሟቸውን በርካታ ተሞክሮዎች ተናገረ። ለምሳሌ ያህል፣ በሜክሲኮ የሚኖር ጋቢኖ የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር የሰዎችን በር የሚያንኳኳው በአብዛኛው አንዴ ወይም ሁለቴ ብቻ የነበረ ቢሆንም አንድን በር ግን አራት ጊዜ አንኳኳ። በሩን የከፈተለት ሰው፣ ጋቢኖ በሩን በሚያንኳኳበት ጊዜ ሕይወቱን ሊያጠፋ እየተዘጋጀ እንደነበረ ነገረው። ሰውየው እንዲህ ብሏል፦ “ለአራተኛ ጊዜ ስታንኳኳ ገመዱን አንገቴ ላይ አስገብቼ ነበር። ይሁን እንጂ በሩን ለመክፈት ስል ገመዱን አወለቅኩት። ማንኳኳትህን በመቀጠልህ አመሰግንሃለሁ። ማንኳኳቱን ቶሎ ብታቋርጥ ኖሮ ራሴን ሰቅዬ ነበር።”
እንደዚህ የመሰሉ ተሞክሮዎች አንዳንድ ጊዜ የአጋጣሚ ጉዳይ ሊሆኑ ቢችሉም ብዙዎቹ ግን በአጋጣሚ የተከሰቱ እንዳልሆኑ እናውቃለን። ከዚህ ይልቅ የአምላክ መላእክት ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ እየመሩት እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው።—ራእይ 14:6
“የተከበረ ሰው ይባረካል።” የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ማይክል በርኔት ይህንን ንግግር ያቀረበው “ከወንድሞቹ ይልቅ የተከበረ ሰው” ተብሎ የተገለጸውን የይሁዳ ዝርያ የነበረውን ያቤጽን ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም ነበር። ያቤጽ “አቤቱ፤ እንድትባርከኝና ግዛቴንም እንድታሰፋ እለምንሃለሁ። እጅህ በእኔ ላይ ትሁን፤ ከሥቃይና ከጕዳትም ጠብቀኝ” ብሎ ወደ አምላክ ጸልዮ ነበር።—1 ዜና መዋዕል 4:9, 10
ተማሪዎቹ በጸሎታቸው ላይ የሚፈልጉትን ነገር ለይተው በመጥቀስ፣ በተለይም በጊልያድ የሠለጠኑበትን ዓላማ እንዲያሳኩ አምላክ እንዲረዳቸው በመጠየቅ የያቤጽን ምሳሌነት ሊኮርጁ ይችላሉ። በተጨማሪም ከክፉ ነገሮች ሙሉ በሙሉ እንዲከልላቸው ባይጠይቁም እንኳ በሐዘን ወይም በክፉ ነገሮች ስሜታቸው እንዳይጎዳ በመርዳት ከሥቃይና ከጉዳት እንዲጠብቃቸው አምላክን መለመን ይችላሉ። አምላክ የያቤጽን ጸሎት እንደመለሰለት ሁሉ ለጊልያድ ተማሪዎችም እንደዚሁ እንደሚያደርግ ጥርጥር የለውም።
“እሳታችሁ መንደዱን እንዲቀጥል አድርጉ።” የጊልያድ አስተማሪና የትምህርት ኮሚቴ ረዳት የሆነው ማርክ ኑሜር ንግግሩን ያቀረበው በ1 ተሰሎንቄ 5:16-19 ላይ ተመርኩዞ ነው። ቃል በቃል እሳት መንደዱን እንዲቀጥል ማገዶ፣ ኦክሲጅንና ሙቀት እንደሚያስፈልገው ሁሉ ተማሪዎቹም ለአገልግሎት ያላቸው ቅንዓት እንዳይጠፋ ሦስት ነገሮች ያስፈልጓቸዋል።
አንደኛ፣ “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ።” (1 ተሰሎንቄ 5:16) ተማሪዎቹ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት መቻላቸው በረከት መሆኑን በማሰላሰል ደስታ ማግኘት ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ ቅንዓታቸውን ያቀጣጥለዋል። ሁለተኛ፣ “ያለማቋረጥ ጸልዩ።” (1 ተሰሎንቄ 5:17) ጸሎት እሳቱ እንዳይጠፋ ከሚያደርገው ከኦክሲጅን ጋር ይመሳሰላል። የልባችንን አውጥተን ለአምላክ በመናገር ረጅም ጸሎት ማቅረብ ይኖርብናል። ሦስተኛ፣ “ስለ ሁሉም ነገር አመስግኑ።” (1 ተሰሎንቄ 5:18) አመስጋኝ የሆነ ልብ ከይሖዋና ከወንድሞቻችን ጋር ያለን ዝምድና ሞቅ ያለ እንዲሆን ያደርጋል። ወንድም ኑሜር “ቀዝቃዛ ከሆነው የተቺነት መንፈስ በተቃራኒ ሞቅ ያለ የአድናቆት ስሜት ይኑራችሁ” በማለት ተናግሯል።
“ይሖዋን ከሰማያት ጋር አብሮ ማወደስ።” የቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች አስተማሪ የሆነው ሳም ሮበርሰን ንግግሩን የጀመረው ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ለይሖዋ ውዳሴ እንደሚያቀርቡ የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች በመጥቀስ ነበር። (መዝሙር 19:1፤ 89:37፤ 148:3) ተማሪዎቹ በሥልጠናው ወቅት ይሖዋን የማወደስ መብት አግኝተው እንደነበረ ተናገረ፤ ከዚያም በቅርቡ በመስክ አገልግሎት ላይ ያገኟቸውን ተሞክሮዎች በሠርቶ ማሳያ መልክ እንዲያቀርቡ አደረገ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ተማሪ መኪና እየነዳ ሳለ በተሽከርካሪ ወንበር የሚሄድ አንድ ሰው እንዲሻገር ለማድረግ መኪናውን ሲያቆምለት ሰውየው አመስግኖት አለፈ፤ ተማሪውም ሰውየው ይህን በማድረጉ አመሰገነው። ከዚያም ውይይት የጀመሩ ሲሆን ሰውየው መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንዲያጠና የቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ። የጊልያድ ተማሪው በቀጣዮቹ ሳምንታት ሰውየውን በሚያስጠናበት ወቅት ሰውየውን ሊጠይቁ ለመጡ ብዙ ሰዎች የመመሥከር አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። መጀመሪያ ላይ ከዚህ ሰው ጋር የተደረገው ውይይት ውሎ አድሮ ሌሎች ሰባት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንዲጀምሩ ምክንያት ሆኗል።
“በመለኮታዊ ትምህርት አማካኝነት እየጠነከራችሁ ሂዱ።” የሕትመት ኮሚቴ ረዳት የሆነው ዶናልድ ጎርደን ከተመራቂዎቹ መካከል ለሁለት ባልና ሚስቶች ቃለ ምልልስ አደረገላቸው። ቃለ ምልልስ ከተደረገላቸው ወንድሞች መካከል አንዱ በትምህርት ቤቱ ላይ ኤፌሶን 3:16-20 ጎላ ተደርጎ እንደተገለጸ አስታወሰ። ይህም ተማሪዎቹ ትሑትና በቀላሉ የሚቀረቡ በመሆን እንዲሁም ይሖዋ ለእያንዳንዱ አገልጋዩ ሊሰጠው የሚችል ብዙ ሥራ እንዳለው በመገንዘብ ‘እንዲጠነክሩ’ ረድቷቸዋል። አንደኛዋ እህት ደግሞ፣ አንድ የጊልያድ አስተማሪ ተማሪዎቹን ለማደግ የሚያስችል ቦታ በሌለው አንድ ትንሽ ጎድጓዳ ሳሕን ላይ ባለ ውኃ ውስጥ እንደሚገኝ ትልቅ ዓሣ ሳይሆን በአንድ ትልቅ ውቅያኖስ ውስጥ እንዳለ ትንሽ ዓሣ እንዲሆኑ ያበረታታበት መንገድ እንዳስደነቃት ገልጻለች። እንዲህ ብላለች፦ “በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ራሴን ከሁሉ እንደማንስ አድርጌ በመቁጠር የምመላለስ ከሆነ ይሖዋ በመንፈሳዊ እንዳድግ እንደሚረዳኝ ከዚህ ምሳሌ ተምሬያለሁ።”
“ይሖዋ በመልካም ያስባችሁ።” የፕሮግራሙን ዋና ንግግር ያቀረበው የበላይ አካል አባል የሆነው ማርክ ሳንደርሰን ሲሆን ጭብጡ የተወሰደው “አምላኬ ሆይ፤ በቸርነት አስበኝ” ከሚለው የነህምያ ጸሎት ላይ ነበር። (ነህምያ 5:19፤ 13:31) ነህምያ ይሖዋ እሱንም ሆነ በአምላክ አገልግሎት ያከናወነውን ሥራ ይረሳል የሚል ፍርሃት አልነበረውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በፍቅር እንዲያስታውሰውና እንዲባርከው መለመኑ ነበር።
በተመሳሳይም ተማሪዎቹ በጊልያድ የተማሯቸውን መሠረታዊ ትምህርቶች በሥራ ላይ ካዋሉ ይሖዋ በመልካም እንደሚያስታውሳቸው መተማመን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋን እንዲያመልኩት የሚያነሳሳቸው ዋነኛ ምክንያት ለእሱ ያላቸው ልባዊ ፍቅር መሆን ይኖርበታል። (ማርቆስ 12:30) አብርሃም ይሖዋን በሙሉ ልቡ ይወድ ስለነበረ አምላክ በፍቅር አስታውሶታል። አብርሃም ከሞተ ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላም እንኳን አምላክ አብርሃምን “ወዳጄ” በማለት ጠርቶታል።—ኢሳይያስ 41:8
ቀጥሎ ወንድም ሳንደርሰን ተማሪዎቹ ባልንጀራቸውን፣ በተለይም ክርስቲያን ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን እንዲወዱ አሳሰባቸው። (ማርቆስ 12:31) “በዘራፊዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ ሆኖ ከተገኘው” ደግ ሳምራዊ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ተማሪዎቹም እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ለመርዳት ቅድሚያውን መውሰድ ይኖርባቸዋል። (ሉቃስ 10:36) ወንድም ሳንደርሰን ነጥቡን ግልጽ ለማድረግ የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግል የነበረውን የጊልያድ ምሩቅ ኒኮላስ ኮቫላክን እንደ ምሳሌ ጠቀሰ። ወንድም ኮቫላክ በግለቱና በፍቅሩ ይታወቅ ነበር። በአንድ ወቅት አንድን ተጓዥ የበላይ ተመልካችና ሚስቱን በአገልግሎት ትጉ እንዲሆኑ ለማበረታታት “ከቀኑ የመጀመሪያውን ክፍል፣ ከሳምንቱ የመጀመሪያዎቹን ቀናት፣ ከወሩ የመጀመሪያዎቹን ሳምንታት፣ ከዓመቱም የመጀመሪያዎቹን ወራት” መጠቀም ጥሩ መሆኑን በመጥቀስ መከራቸው። እህትን ለጥቂት ቀናት ከተመለከታት በኋላ ግን “የነገርኩሽን እርሺው። አንቺ ቀድሞውንም ቢሆን ጠንክረሽ እየሠራሽ ነበር። ይሖዋን እያገለገልሽ መቀጠል እንድትችይ ቀስ በይ” አላት። ይህ ወንድም በደግነትና በርኅራኄ የሰጣት ምክር ይህች እህት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለብዙ አሥርተ ዓመታት እንድትቀጥል ረድቷታል።
በመጨረሻም ወንድም ሳንደርሰን ተማሪዎቹ ሌሎችን በማስተማርና በማሠልጠን የተማሩበትን ዓላማ እንዲያሳኩ አበረታታቸው። (2 ጢሞቴዎስ 2:2) በተመደቡበት ቦታ በማገልገል የወንድማማች ማኅበሩን በሚያጠናክሩበት ወቅት ይሖዋ በመልካም እንደሚያስባቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።—መዝሙር 20:1-5
መደምደሚያ። ተማሪዎቹ ዲፕሎማቸውን ከተቀበሉ በኋላ ከመካከላቸው አንዱ ተመራቂዎቹን ወክሎ የአድናቆት መግለጫ ደብዳቤ አነበበ። ከዚያም ከተመራቂዎቹ መካከል አሥራ አምስቱ ለይሖዋ ዘምሩ ከተባለው የመዝሙር መጽሐፍ ላይ “እረኞች—ስጦታ የሆኑ ወንዶች” የሚል ርዕስ ያለውን መዝሙር ቁጥር 123ን በድምፃቸው ብቻ በመዘመር ፕሮግራሙን አስደሳች በሆነ መንገድ ደምድመዋል።